የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው - አቶ አደም ፋራህ
ሚዛን አማን ግንቦት 07 / 2015 (ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሁለተኛ ዙር ክልላዊ የበልግ ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቤንች ሸኮ ዞን ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው በይፋ የተጀመረው።
በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ ፋኒቃ ቀበሌ በመገኘት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት አቶ አደም እንዳሉት የአረንጓዴ ልማት ሀብቶቻችን ላይ እሴት በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
"አረንጓዴ አሻራ ከአየር ንብረት ሚዛን ማስጠበቅ ባሻገር የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንደ ሀገር እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በዚህም ተግባር በየዓመቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ከዘርፉ የፍራፍሬና መሰል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን ለማግኘት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከሀገር ሉዓላዊነትና ከህልውና ጋር የሚተሳሰር በመሆኑ የደን ልማት ሥራውን ከዚሁ ጋር አስተሳስሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደንን ከኑሮው ጋር አስተሳስሮ የመምራት የረጅም ዓመት ታሪክ ያለው መሆኑን በንግግራቸው አንስተዋል።
ኅብረተሰቡ ይህንን ደን የመጠበቅ መልካም ባህል እንዲያጎለብት ማበረታታትና መደገፍ ይገባል ያሉት አቶ አደም፣ ደንን ሳያጠፉ ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ክልሉ ጥራት ያላቸው የቡና፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎች የግብርና ውጤት የሆኑ የኤክስፖርት ምርቶች በስፋት የሚመረትበት ክልል መሆኑን አመላክተዋል።
በይበልጥ የክልሉን ብሎም ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዘርፉን ከፍ ለማድረግ የአካባቢውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትን ከሰው ኃይል አቅም ጋር በማስተሳሰር አልምቶ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው በክልሉ ሁሉም ዞኖች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው የችግኝ አይነቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ የአረንጎዴ አሻራ ልማት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አሰታውቀዋል።
የክልሉ ህዝብ የደን አጠባበቅ ልምድ እየሰፋ ከመጣው የመልማት ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ምርት እንዲሁም ሌሎች የኢኮኖሚ መሠረት ያላቸው ችግኞች እየለሙ ነው ብለዋል።
ደን ያለውን ከፍተኛ ጥቅም ኅብረተሰቡ ተረድቶ የጥበቃና እንክብካቤ እንዲያጠናክር ግንዛቤ የመፍጠርና የማበረታታት ሥራ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው አካባቢው ያለውን ምቹ የአየር ጸባይ መሠረት በማድረግ በዓመት ሁለት ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልሉ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በበልግ ወቅት ሁለተኛ ዙር የተከላ መርሐ ግብር ከ54 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እስከ ሰኔ 30/2015 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚተከሉ ተናግረዋል።
በ2014 ዓ/ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል በአጠቃላይ የ175 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 199 ሚሊዮን ችግኝች በላይ በመትከል ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉንም አቶ ማስረሻ አስታውሰዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።