ቀጥታ፡

ኢዜአ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ቋንቋዎች የአገር ገጽታን ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በውጭና በአገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲሁም ብቃት ባላቸው ሙያተኞች የአገር ገጽታን ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሠራተኞች መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይ የአስረጂዎች መድረክ አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ረቂቅ ደንቡ የተዘጋጀበትን ምክንያትና አስፈላጊነት አብራርተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በማብራሪያቸው ተቋሙ የአገር ገጽታን ለመገንባት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ፣ ተዓማኒና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭነቱን ለማጠናከርና አገራዊ መግባባትን ለማምጣት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አስረድተዋል።

ኢዜአ በ2022 ዓ.ም ግቡ ከአፍሪካ ቀዳሚና ተወዳዳሪ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ለዚህም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመዝለቅ አሠራርን ማዘመን፣ ለተልዕኮ መሳካት በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ቋንቋዎች በብቃት የሚሰራ የሰው ኃይል ማፍራት በማስፈለጉ የሠራተኞች መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ተቋሙ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የያዘውን ትልቅ ራዕይ ለማሳካት ብቁ ሙያተኞችን የማፍራትና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂን ለመጠቀም  የሚያስችል አቅም እያዳበረ ነው ብለዋል።

ለዚህም አገልግሎቱ የመረጃ ምንጭ እንደመሆኑ ተዓማኒ፣ የተደራጀ፣ አስተማማኝ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ በሙያና በብቃት የዳበረ የሰው ኃይል በማስፈለጉ የሠራተኞች መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ደንቡ የተቋሙን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ቁርጠኛ የሆኑ፣ ልዩ ችሎታና እውቀት ያላቸው፣ በስነ-ምግባር የታነፁ ሙያተኞችን ለማፍራትና ለማስተዳደር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በመሆኑም ተቋሙ እስካሁን ሲጠቀምበት ከነበረው የሲቪል ሰርቪስ መመሪያና ደንብ ወጥቶ ሚዲያነቱን ታሳቢ ያደረገ ደንብ በማስፈለጉ የአገር ውስጥና የውጭ የሚዲያ ተቋማትን ተሞክሮ በማየት ደንቡ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

የሠራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የሥራ ስምሪትና አፈጻጻም ውጤታማነት እንዲሁም ከሕግና አሠራር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እውን ለማድረግ ደንብ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ደንቡ ተግባር ላይ ሲውል ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ሚዲያ ባህሪውን የተረዳ ሙያውን በቁርጠኝነት የሚተገብር የሰው ኃይል ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት ።

እየተለዋወጠ የመጣውን የሚዲያ ኢንዱስትሪ ታሳቢ ያደረገ፣ ተወዳዳሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሰው ኃይልና የሙያ አቅም ለመፍጠር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚመራበት የመተዳደሪያ ደንብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት በተለያዩ ቋንቋዎች እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ተቋሙ በቅርቡ በእንግሊዝኛ እና በአረቢኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለመጀመር እየተዘጋጀ በመሆኑ ሙያተኞችን ለማግኘት ደንቡ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።


 

ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ ደንቡ ላይ ከአገላለጽና ትርጉም ማብራሪያና ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው አንቀጾች ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስቷል።

የተቋሙ ኃላፊዎች ቋሚ ኮሚቴው እንደ አስተያየት ያነሷቸውን ሀሳቦች በመውሰድ ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም