ቀጥታ፡

በልጅነቴ የማውቀው ሃላላ ኬላ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት መልማቱ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል - ፖለቲከኛዋ ዶክተር ራሔል ባፌ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ከሰሞኑ የኮይሻ ገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል የሆነውንና በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

ከጎብኚዎቹ መካከል ፖለቲከኛዋ ዶክተር ራሔል ባፌ ይገኙበታል።

ዶክተር ራሔል ትውልድና ዕድገታቸው ድንቅ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር በተቸረው የዳውሮ ዞን በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሀላላ ኬላ አካባቢ ነው።
 

በልጅነታቸው ምቹ ትምህርት መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ከዳውሮ ወደ ወላይታ ሶዶ ወይም ወደ ጅማ ከተማ ርቀው መሄድ ይገደዱ እንደነበር ዶክተር ራሔል ያወሳሉ። 

የመንገድ መሰረተ ልማት አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳደረገው ጠቁመው ከዳውሮ ዞን ከተማ ወደ ወላይታ ሶዶ ለመድረስ ለሶስት ቀን በእግር ይሄዱ እንደነበር ገልጸዋል።

የኦሞን ወንዝ አቋርጠው ከዳውሮ ወደ ወላይታ ለመሻገር አንድ አነስተኛ ድልድይ እንደነበረች አስታውሰው፤ ዛሬ ግን ሌላ መልክ መያዙ አስደንቋቸዋል።

ዶክተር ራሔል በልጅነታቸው በእግራቸው የተሻገሩት የኦሞ ወንዝ ዛሬ ላይ በግልገል ጊቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ተውጦ በጀልባ ተሻግረው፤ የሀላላ ኬላ እሴት ተጨምሮበት ልዩ ገጽታውን ማየት ችለዋል።

ሀላላ ኬላ ታሪካዊ ሥፍራ በኦሞ ወንዝ ላይ በተገነባው የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ሌላ ድምቅት ሆኖት፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ሰው ሰራሽ ሐይቁ ተሰናስነው አካባቢው ልዩ ገጽታ ተላብሷል።

'ሃላላ ኬላ ለዳውሮ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ ቅርስ ነው' የሚሉት ዶክተር ራሔል፤ የዳውሮ ነገስታት ለብዙ ዓመታት ዳውሮን ከጠላት ለመጠበቅ ያሰሩትና በመጨረሻው የዳውሮ ንጉስ ሃላላ መሰየሙን ያነሳሉ። 

ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል ሆኖ የሃላላ ኬላ ለቱሪስት መዳረሻነት መልማቱ ለአካባቢውና ለአገሪቷ ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት በጎ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። 

አያሌ የልጅነት ትዝታ የሰነቁበትና ውጣ ውረዶችን ያዩበት መልክዓ ምድር በዚህ ደረጃ ለምቶ ማየታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም።

በተለይም ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመሆን መጎብኘታቸውም እንዳስደሰታቸውም ነው ዶክተር ራሔል የገለጹት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም