የበልግ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው- የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የበልግ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው- የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2015 (ኢዜአ)፦ የበልግ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በድርቅ የተጎዱትን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የበልግ ዝናብ እየዘነበ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።
ይህንን ተከትሎም በተለይ ደራሽ ጎርፍና መሰል አደጋዎች እየተከሰቱ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተለይም በድርቅ ተጎጂ የነበሩ የኦሮሚያ፣የሶማሌና የደቡብ ክልል አካባቢዎችን ጨምሮ በሰባት ክልሎች በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ ያደረሰው የጎርፍ አደጋ በሰብልና እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
በዚህም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
መንግስት የብሔራዊ የጎርፍ መከላከልና የአደጋ ምላሽ ሰጪ ግብረ ኃይል አቋቁሞ በአካባቢዎቹ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
አደጋው ወደደረሰባቸው አካባቢዎች የተላከው የባለሙያዎች ቡድንም የአደጋውን ሁኔታ ቅኝት ማድረጉንና ሰብዓዊ ድጋፎችም ለተጎጂዎች ተደራሽ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጎርፍ አደጋው በሰው፣እንስሳት፣ሰብልና ንብረት ላይ ያደረሰው የጉዳት መጠን ጥናት ተደርጎ ይፋ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
መንግስት በጎርፍ አደጋ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከልና ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በቀጣይ ድርቅንና ጎርፍን መከላከል እንዲሁም መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎችን በዘላቂነት ለማከናወን የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት አባል የሆኑ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በድርቅ በተከታታይ በተጎዱ አካባቢዎች እየዘነበ ያለውን የበልግ ዝናብ የማከማቸትና ለሰብልና ለእንስሳት የመጠቀም ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።