ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

በመርሐ-ግብሩ መሰረት አርባ ምንጭ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አርባ ምንጭ ከተማ በ24 ነጥብ 14ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል፤ ወላይታ ድቻ በ31 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፤ ሁለቱን ተሸንፎ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በአንዱ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ24ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሀዲያ ሆሳዕና በ32 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በ28 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።

ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮ ኤሌክትሪክን እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም