በሲዳማ ክልል የባህርዛፍ ተክልን በማስወገድ በሌላ የአፈር ለምነትን በሚያስጠብቁ ተክሎች የመተካት ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የባህርዛፍ ተክልን በማስወገድ በሌላ የአፈር ለምነትን በሚያስጠብቁ ተክሎች የመተካት ስራ እየተሰራ ነው
ሀዋሳ ግንቦት 06/2015 (ኢዜአ).... በሲዳማ ክልል የባህርዛፍ ተክልን በማስወገድ በሌላ የአፈር ለምነትን በሚያስጠብቁ ተክሎች የመተካት ስራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሀላፊና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቅረየሱስ አሸናፊ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የባህር ዛፍ ተክል የመሬት ለምነትን ከሚቀንሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል።
የባህር ዛፍ ተክል ውሀ አዘል መሬቶችን እንዲያደርቅ ታስቦ ይተከል እንደነበር አስታውሰው፤ ነገር ግን የመሬት ለምነትን በመቀነስ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድርና የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ሲጎዳ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ ብሎም አርሶ አደሩ ከባህርዛፍ ይልቅ የአፈር ልምነትና ሥነ ምህዳርን የማስተካከል እንዲሁም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ያላቸው ተክሎችን ለማልማት ሕጋዊ ማዕቀፍ ያለው አሰራር በማበጀት ወደስራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ባህርዛፍ ሌሎች ተክሎችና ምርታማ አፈርን በማይጎዳበት ቦታ ብቻ እንዲተከል የሚደነግግ አዋጅ በክልሉ ምክር ቤት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 27/2015 በተያዘው በጀት ዓመት መፅደቁን ተናግረዋል፡፡
አዋጁን መሰረት በማድረግም ባህርዛፍን የማስወገድ ስራ በትኩረት መጀመሩን ገልጸው፤ እስካሁን 4 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የነበረው ባህርዛፍ ተወግዶ በሌሎች ሰብሎች መተካቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች በሚባል ደረጃ የባህርዛፍ ተክል በስፋት እንደሚገኝ ጠቅሰው በአብዛኛው ለም፣ ውሀ አዘልና፣ ሌላ ተክል ቢተካበት ምርታማ መሆን የሚችል መሬት ላይ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
ክልሉ ካለው የመሬት ጥበትና የህዝብ ጥግግት አኳያ ባህርዛፍን ነቅሎ ውጤታማ በሆኑ ሰብሎች በመተካት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
አንድ ያደገ የባህር ዛፍ ተክል በ20 ሜትር ዙሪያ መጠን ውስጥ የሚተከሉ ተክሎችን የሚጎዳና መሬት እንደሚያደርቅ ገልጸዋል።
ባህርዛፍ ጥቅም ላይ ለመዋል በትንሹ አምስት ዓመት ይፈጅበታል ያሉት አቶ ፍቅረኢየሱስ፤ ጥቅሙ በአጭር ጊዜ ከሚደርሱና የአፈር ለምነትን ከማይጎዱ ሰብሎች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዋጁ መሠረት የባህርዛፍ ተክል መትከል የሚቻለው ከእርሻና ከግጦሽ መሬቶች በራቀ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎችን ማልማት በማይቻልበት ቦታ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ባህርዛፍን ከማሳቸው በማስወገድ በሌላ ተክል ከተኩ አርሶ አደሮች መካከል በአለታ ወንዶ ወረዳ ዶንጎራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደረ ማርቆስ ኔቶ ባህርዛፍን ከማሳቸው አስወግደው በቡና ችግኝ መተካታቸውን ገልጸዋል።
ከእርሳቸው ጋር ኩታ ገጠም ከሆኑ ሌሎች ስድስት አርሶ አደሮች ጋር በመሆን 4 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ባህር ዛፍ አስወግደው በሌላ ሰብል መተካታቸውን ተናግረዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት የቡና ተክል በማንሳት ባህር ዛፍ እንደተከሉ አስታውሰው፤ ሆኖም ባህርዛፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ሆኖ እንዳገኙት ጠቁመዋል።
የደራራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ኤልያስ ጋሳ በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር በሚሆን ማሳቸው ላይ የነበረውን የባህር ዛፍ ተክል በማስወገድ በሰብሎች መተካታቸውን ገልፀዋል፡፡
ባህርዛፍ በነቀሉበት ቦታ በቆሎ፣ ቦሎቄና ድንች መትከላቸውን የተናገሩት አርሶ አደር ኤልያስ፤ ባህርዛፍ የሚያስከትለውን ጉዳትና ከሌሎች ሰብሎች የምናገኘውን ጥቅም አሁን ተረድተናል ብለዋል፡፡
በአካባቢ ማህበረሰብ ተሳትፏዊ ውሳኔ የሚተገበረው የባህር ዛፍ አተካከልና አወጋገድ አዋጅ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በመመልከት ተክሉ ከየት ከየት አካባቢ መነሳት እንዳለበት የሚወስንበትና በወረዳ ምክር ቤቶች ፀድቆ ተግባራዊ የሚደረግበት አሥራር መኖሩን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።