የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበው መስራት በመጀመራቸው በሃሳብ ልዕልና የሚመራ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል እየዳበረ መጥቷል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበው መስራት በመጀመራቸው በሃሳብ ልዕልና የሚመራ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል እየዳበረ መጥቷል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ ግንቦት 06/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበው መስራት በመጀመራቸው በሃሳብ ልዕልና የሚመራ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል እየዳበረ መምጣቱን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኔዘርላንድ መልቲ-ፓርቲ ሲስተም ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
ከምክክር መድረኩ በተጓዳኝም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በሀላላ ኬላ የተገነባውን ዘመናዊ የቱሪስት መስህብ ጎብኝተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የፓርቲ አመራሮች የኢትዮጵያን መፃዒ ተስፋ የተሻለ ለማድረግ ፖለቲከኞች ከቁርሾና ጥላቻ ይልቅ በመቀራረብ በሃሳብ ልዕልና አሸናፊ ለመሆን መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ መቀራረብና አብሮነት በሃሳብ ልዕልና የመመራት አዲስ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ ፓርቲዎች የሃሳብና የመስመር ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ጉዳይ ግን ወጥ አቋም መያዝ ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ራሔል ባፌ፤ አጥፍቶ ከመጥፋትና በጦር ኃይል ከማመን ይልቅ በሃሳብ የበላይነት በማመን በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን የመፍታት ልምድ እየዳበረ መሄድ አለበት ብለዋል።
በትብብርና አብሮነት የኢትዮጵያን ዕምቅ ሃብት በማልማት ወደፊት የምንራመድበት እንጂ በልዩነት ሰላም እንዲርቅ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አብዱራህማን መሃዲ፤ በአሁናዊ ፖለቲካ ለሀገር ግንባታ የሚበጅ መቀራረብና የትብብር መንፈስ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት መሀመድ የኑስ፤ አሁን ላይ የሚያስፈልገው በሃሳብ ልዕልና አሸናፊ መሆን እንጂ ግጭትና ጦርነት ምንም ዓይነት መፍትሔ የማያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው መቀራረብ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መሰረት እየጣለ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ተሰማ ኤልያስ እና የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን ታፈሰ፤ የፓርቲዎች መቀራረብ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳለጥ ይበጃል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮነትና መቀራረብ ባህል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚያደርጉት የምክክር መድረክም አዲስ የዴሞክራሲ ባህል መሰረት እያኖረ መሆኑን ጠቅሰዋል።