ቀጥታ፡

የግብርና እና ሳይንስ አውደ-ርዕዩ ለግብርናው ዘርፍ ፈጣን እድገት የሚያግዙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበት ነው  -ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2015(ኢዜአ)፡- በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የግብርና እና ሳይንስ አውደ-ርዕይ ለግብርናው ዘርፍ ፈጣን እድገት የሚያግዙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበት መሆኑን የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

የግብርና ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና ኢትዮ-ቴሌኮም "ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ" በሚል መሪ ሃሳብ በጋራ ያዘጋጁት የግብርና እና ሳይንስ አውደ-ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

በአውደ-ርዕዩ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ዘመናዊ የሆኑ ወጪና ጊዜ ቆጣቢ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የልምድ ልውውጥ እያደረጉበትና የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ልዩ አጋጣሚ ሆኗል።

ከሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም ለዕይታ ክፍት የተደረገውንና ለአንድ ወር የሚቆየውን የግብርና እና ሳይንስ አውደ-ርዕይ በማስመልከት ኢዜአ ተሳታፊዎችን አነጋግሯል::
ከአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች መካከል ከሬንሲስ ኢንጂነሪግ ድርጅት ለሚ አሰፋ፤ በፀሐይ ኃይል ውሃ መሳብ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለዕይታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

የቴክኖሎጂ ውጤቱ በተለይም በገጠር አርሶ አደሮች የፀሐይ ብርሃን ተጠቅመው በቀላሉ ውሃ ለመሳብ የሚያስችላቸው  መሆኑን አብራርተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር በኩልም የተቀናጀ የዓሳ እርባታ ዘዴን ማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለዕይታ ቀርቧል።


 

በሚኒስቴሩ የዓሳ ሃብት ባለሙያዋ አቻምየለሽ ቱሬሳ፤ የቴክኖሎጂ ውጤቱን በማስመልከት ሲያብራሩ ዓሳን፣ ዶሮንና አትክልትን በአንድ አነስተኛ ሥፍራ ማምረት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በተለይም የሌማት ትሩፋትን በዘመናዊ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግና ለከተማ ግብርና ልማት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ አስረድተዋል።

የቆላ ዝንብ ማራባትና ማምከን ፕሮጀክት የኤስ አይ ቲ ዴስክ ኃላፊ ሞገስ ሂዶቶ፤ በቴክኖሎጂ በታገዘ የላቦራቶሪ ምርምር የቆላ ዝንብን ለማጥፋት የሚያስችል ቤተ-ሙከራ በአዲስ አበባ መቋቋሙን ገልጸዋል።


 

የተቋቋመው ቤተ-ሙከራም ከኢትዮጵያ አልፎ ለ38 የአፍሪካ አገራት ጥቅም እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የቆላ ዝንብን ማጥፋት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት ለዕይታ መቅረቡን ገልጸው፤ ኤግዚቢሽኑ ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅና ተደራሽነትን ለማስፋት ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን አብራርተዋል።

አዳዲስ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ቴክኖሎጂን ለዕይታ ይዘው መምጣታቸውን የገለጹት ደግሞ በእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የአባላዘር ማምረቻ ላቦራቶሪ የቤተ-ሙከራ ባለሙያ  ሚሊዮን አድማሱ ናቸው።


 

ኢንስቲትዩቱ የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን ለዚሁ ተግባር የሚውልና በወተት ምርታቸው የታወቁ የውጭ አገር የከብት ዝርያዎችን ከአገር ውስጥ ጋር ማዳቀል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በዚህ ቴክኖሎጂ ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ ኤግዚቢሽኑ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በኤግዚቢሽኑ ከ70 በላይ የምርምርና ፈጠራ ሥራዎች፣ ዲጂታላይዜሽን ግብርና እና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም አውደ-ርዕዩን በይፋ መክፈታቸው ይታወቃል።

 

 

 

 

 

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም