ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በዘመናዊ  ቴክኖሎጂ የታገዘ አደጋን መከላከል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2015 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ  አደጋን መከላከል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ   ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።   

የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በዓለም ለ24ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ ተከብሮ የዋለውን  የእሳት አደጋ ሠራተኞች ቀን በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አክብሯል።


 

እለቱ " የሚጠብቁን ጀግኖችን እናክብር " በሚል መሪ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአደጋ ጊዜ ባለሙያዎች በተገኙበት ተከብሯል።

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ አደጋን መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ ተቋም፣ የሰው ኃይልና የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ መሆኑን ገልጸዋል። 

የእሳትና ድንገተኛ አደጋን መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ ተቋም ለመገንባት ቀደም ሲል የለውጥ ሥራ መከናወኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የከተማዋን እድገት የሚመጥን በሰው ኃይልም ይሁን በቴክኖሎጂ አደጋን መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር እውን ሆኗል ብለዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል በቴክኖሎጂም ይሁን በሰው ኃይል በዘመናዊ መልኩ እንዲደራጅ መደረጉን ገልጸዋል።

በመዲናዋ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እያደረጉት ላለው የላቀ ተግባርም ከንቲባዋ አመስግነዋል።

 የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሰሐ ጋረደው በበኩላቸው፤ በከተማዋ የአደጋ ተጋላጭነት ስጋት ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በቴክኖሎጂ በመታገዝ  ብቃት ያለው ባለሙያዎችን በማፍራት ሌት ተቀን አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ከተቋሙ አመራርና ሠራተኞች መካከል ሙሉጌታ ውዱ እና አደም ተማም እለቱ ሲከበር እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ እውቅና በመሰጠቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የተሰጣቸው ምስጋና እና እውቅና በቀጣይም ለላቀ ሥራ የሚያዘጋጃቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም