በአማራ ክልል በበልግ ሰብል ከለማው መሬት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በበልግ ሰብል ከለማው መሬት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ
ባህር ዳር፣ ግንቦት 6/2015 (ኢዜአ):-በአማራ ክልል በበልግ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የበልግ ወቅት 230 ሺህ 312 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ይገኛል።
በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 218 ሺህ 722 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው፤ የበልጉ ዝናብ በስርጭትም ሆነ በመጠን የተሻለ በመሆኑ ከዕቅድ በላይ ማልማት መቻሉን ገልፀዋል።
በበልግ ከለሙ ሰብሎች መካከልም ገብስ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሾ፣ በቆሎ፣ ቅመማቅመም፣ ጥራጥሬና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ለበልግ ሰብል ልማት ከ2 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ኮምፖስት፣ ከ11 ሺህ 500 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳሪያ፣ 450 ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።
በዚሁ የበልግ ልማት ከ215 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአርሶ አደሮቹ ከለማው መሬት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።