የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል
አዲስ አበባ ግንቦት 6/ 2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ31 ነጥብ 9ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ነጥብ 15ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
አንዱን ተሸንፎ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሶስት ጊዜ ተሸንፏል ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 4 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የ24ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በአዳማ ከተማና ባህር ዳር ከተማ መካከል ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ይደርጋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ አዳማ ከተማ በ32 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
አዳማ ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።
ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ይችላል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐግብር እስከ ግንቦት 9/2015 ይቆያል።