የክረምት ወቅት የአየር ትንበያ መረጃን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት ወቅት የአየር ትንበያ መረጃን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ማዋል ይገባል
አዳማ ግንቦት 5/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቀርበውን የክረምት ወቅት የአየር ትንበያ መረጃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስኬታማነት መጠቀም እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ አሳሰቡ።
የበልግ አየር ሁኔታ ትንበያ ግምገማና የመጪው ክረምት የአየር ትንበያ የምክክር መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳስገነዘቡት ባለድርሻ አካላት ኢንስቲትዩቱ ወቅትን ተከትሎ የሚያቀርበውን የአየር ሁኔታ ትንበያ በመከታተል በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል።
ይህም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ኢንስቲትዩቱ የሚያሰራጨው የአየር ትንበያ መረጃ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኝ ባለድርሻ አካላትና ተጠቃሚው ማህበረሰብ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የአየር ትንበያን መረጃ መሰረት በማድረግ በተከናወኑ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በአገር ላይ ሊደርሱ የነበሩ ችግሮችን መቋቋም እንደተቻለም ገልጸዋል።
በመድረኩ በበልግ ዝናብ ትንበያ የነበረውን ውጤታማነትና የታዩ ክፍተቶችን ለይቶ ለቀጣይ የክረምት ወራት የአየር ሁኔታ ትንበያ ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው በመጪዎቹ የክረምት ወራት ከ85 በመቶ በላይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል።
ዝናቡም ለግብርና ልማት፣ ለተፋሰስ ልማትና ለግድቦች ውሃ ሙሌት እንደሚረዳ አስረድተዋል።
የክረምት የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በአግባቡ ደርሶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በክረምቱ የሚኖረውን የዝናብ ውሃ በማቆርና በመያዝ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚከሰትባቸውን አካባቢዎች ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
የክረምቱ ዝናብ በከተሞችና በተፋሰሶች አካባቢዎች አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አቶ ፈጠነ አሳስበዋል።
"የጎርፍ ማውረጃ ቦዮች ጽዳት፣ የጎርፍ መከላከልና የወንዞች አስተዳደር ላይ ከወዲሁ ቅድመ ጥንቃቄን መሰራት ያደረጉ ተግባራት ሊከናወንባቸው ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።
በበልግ የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃ አጠቃቀም የተሻለ ውጤታማነት መታየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ለእዚህም በበልግ አየር ሁኔታ ትንበያ በቅድመ ጥንቃቄ የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል።