ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ከበልግ እርሻ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል- የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ

ሐዋሳ ግንቦት 05/2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል በበልግ ወቅት  ከሚለሙት ዋና ዋና ሰብሎችና ሥራ ሥር ተክሎች ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ተገቢውን ግብዓት ተጠቅመው ያለሙት የበልግ ሰብል በምርት ይዘቱና አቋሙ ተስፋ ሰጪና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡


 

በክልሉ ያለውን የበልግ እርሻ አቅም ተጠቅሞ ስኬታማ ለማድረግ አመራሩን፣ ፈጻሚውንና አርሶ አደሩን በማቀናጀት ወደ ተግባር መገባቱን የቢሮው ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ተናግረዋል ፡፡

በዚህም ከ105 ሺህ 117 ሄክታር በላይ መሬት በቆሎ፣ ቦሎቄና ድንችን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ሥር ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 88 በመቶው ያህሉ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ካለው የዝናብና መልካም አየር ጠባይ የተነሳ የምርት አያያዙ ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት አቶ መምሩ፣ በክልሉ የበልግ እርሻ በዋና ዋና ሰብሎችና በሥራ ሥር ዘር ከተሸፈነው መሬት ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል  ብለዋል፡፡

ከበልግ ልማቱ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በቆሎ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ 60 ሺህ ሄክታር ለምቶ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከ11 ሺህ 800 ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘርና 134 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን ገልጸዋል። 

በሐዋሳ ዙሪያና በብላቴ አካባቢ በሚገኙ ቀበሌዎች እስከ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በቆሎ እንደሚዘራም አመላክተዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂዎች መጠቀም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ መምሩ፣ተጨማሪ 30 ሺህ ኩንታል ዩሪያ የተባለውን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማስገባት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ እየተከናወነ ያለው የበልግ እርሻ ስራ ግብርናን በሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዝ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሩ ክትትል በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ በበልግ ወቅት ለማልማት ከታቀደው 60 ሺህ ሄክታር የበቆሎ ማሳ 40 ከመቶው የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም ታርሷል፡፡

በዚህም የጋራ የሆነ የግብዓት አጠቃቀም፣እንክብካቤ፣ የምርት አሰባሰብና የገበያ ትስስር የሚፈጥር የግብርና ልማት በማካሄድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የአረም፣ በሽታና የተባይ ቁጥጥር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው፣ እየጣለ ያለው ዝናብ  አሉታዊ ተፅእኖ በሚፈጥርባቸው አካባቢዎችም ውሃ የማፋሰስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎችም የማሳ ውስጥ የውሃ እቀባ ሥራ በማከናወን የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ በቆሎ ለሚዘሩት ወረዳዎች ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሻመና 01 ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ ታገሰ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ተገቢውን ግብዓት ተጠቅመው ካለሙት በቆሎ ከ600 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። 

የወረዳው ግብርና ባለሙያዎች አዝመራው ከወትሮው በተሻለ ውጤታማ እንዲሆን የግብዓቶች አጠቃቀም ዕውቀት እንዲያገኙ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል፡፡

 የብላቴ ዙሪያ ወረዳ ሃንጃጎሮ ቀበሌ ወጣት አርሶ አደር ጸጋዬ ዱሴ በበኩሉ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ከባለሙያ በተደረገለት ድጋፍ ተገቢውን ግብዓት ተጠቅሞ በግማሽ ሄክታር በቆሎ መዝራቱን ተናግሯል፡፡

ወረዳው ያቀረበለትን ግብዓት ወቅቱን ጠብቆ ካለመው መሬት ከ30 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቅም ገልጿል። 

በክልሉ በበልግ እርሻ 333ሺህ 468 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን፣ በዋና ዋና ሰብሎች በቆሎና ቦሎቄ፣ ከሥራ ሥር ድንችና ስኳር ድንችን ጨምሮ ሌሎችም መልማታቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም