ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ የሠላምና ፀጥታ ሥራዎችን የሚያከናውን የፖሊስ ተቋም መገንባት ወሳኝ ነው 

ሀዋሳ ግንቦት 5/2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ህብረተሰቡን ያሳተፈ ውጤታማ የሠላምና ፀጥታ ሥራዎችን የሚያከናውን የፖሊስ ተቋም መገንባት ወሳኝ መሆኑን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

  የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያዘጋጁት የፖሊስ መኮንኖች ግምገማዊ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የምክክር መድረኩን የመሩት በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ናቸው።

አቶ አለማየሁ በመድረኩ እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በየአካባቢው የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች በሠላማዊ መንገድ ተፈተው የህዝብ ደህንነት እንዲጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሏል።

በእዚህም በአሁኑ ወቅት በክልሉ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት።

በክልሉ ዘላቂ ሠላም ማስፈን እንዲቻል ማህበረሰቡን አስተባብሮ ውጤታማ የሠላምና ፀጥታ ሥራዎችን የሚሰራ የፖሊስ ተቋም መገንባት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የፀጥታ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የሥጋት ደረጃና የሚያስፈልጋቸው የምላሽ መጠን የመለየት ሥራ መሰራቱንም አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

በተለይም የጥፋት ኃይሎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቀጠናዎች ማህበረሰቡን ያሳተፈ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ በበኩላቸው፣ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በማርገብ አካባቢዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ፖሊስ ዓይነተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የተስተዋሉ ጉድለቶች መኖራቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣"ጠንካራዎቹን በማስቀጠልና ጉድለቶችን በማረም ለህብረተሰቡ የተሟላ ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራን ነው" ብለዋል።

በክልሉ ለአደረጃጀት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በመንግስት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው፣በዚህ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ የፀጥታ ሥጋቶችን ለማስቀረት ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል። 

ከቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት አብዛኛዎቹ ወደ መደበኛ ፖሊስ መቀላቀላቸውን የገለጹት ኮሚሽነር አለማየሁ፣ ይህም ለአካባቢያዊ የጸጥታ ሥራ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና ገፅታ ግንባታ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ጁሀር ሙሳ በክልሉ በየአካባቢው በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላትና መደበኛ ፖሊሶች መስዋዕትነትን መክፈላቸውን ገልጸዋል።

"ቀደም ሲል የነበሩ የፀጥታ ችግሮች አሁን ላይ መቀነሳቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም ህብረተሰቡን ያሳተፈ መደበኛ የፖሊስ ሥራን በማጠናከር ህዝብን የሚያረካ ሥራ መስራት ይገባል" ብለዋል።


 

በምክትል ኮሚሽነር ማዕረግ የደቡብ ፖሊስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ኮማንደር አብርሀም ቲርካሶ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ግጭቶች ሲከሰቱ ከአቅም በላይ ናቸው በሚል ሥራውን ለልዩ ኃይል አሳልፎ የመስጠት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት መደበኛ ፖሊስን ጨምሮ በተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች በመደራጀታቸው ተጨማሪ አቅም ስለሚሆኑ ተገቢ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይ አስቀድሞ ወንጀልን መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መስራት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በፖሊስ መኮንኖች ግምገማዊ የምክክር መድረክ ላይ ከኮሚሽኑ እስከ ወረዳና ከተማ ያሉ የፖሊስ አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም