ቀጥታ፡

"በእጅ ያለን ፀጋ ለተሻለ ህይወት"

 በጣፋጩ ሰለሞን

 ሀብት ንብረት ለማፍራት  ነገን ተስፋ አድርጌ አስቀድሜ ያኖርኩት ጥሪት የለኝም፤ሥራ ሰርቼ የነገ ህልሜን ለማሳካት ሥራ የለም፤ ስራ ማግኘት ወጣሁ ወረድኩ ባዘንኩ ግን ሥራ ፈልጌ አጣሁ፤ ሰርቼ መለወጥ እፈልጋለሁ ግን ገንዘብ የለኝም፤ ምን  ይሻለኛል፤ 'ኸረ ወዲያ ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም' ብሎ ማማረር ተገቢ አይደለም፤ ይላሉ አርሶ አደር ቲቲዮስ መንግሥቱ። በከንቱ "ስባክን የኖርኩት በእጄ ያለውን ፀጋ ማየት ሳላልቻልኩ ነው" ሲሉም ያክላሉ። ሥራ የለ፤ ገንዘብ የለ፤ ብሎ በማማረር የነገ መፃሂ ዕድልን አጠውልጎ ከማምከን ይልቅ ቆም ብለን ተፈጥሮ ያለ ስስት ለገሳ የሰጠችንን ሀብትና ፀጋ በመለየት፤ መወሰን፤ መትጋት፣ መታተር፣ በዓላማ መፅናትና በእጃችን ያለን ሀብት በማልማት መለወጥ እንደምንችል ማሰብና በተግባር ማሳየት አለብን ሲሉም ይመክራሉ።

አርሶ አደር ቲቲዮስ መንግሥቱ ትውልድ ዕድገታቸው በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ ጭልሻ ቀበሌ ነው። እንዲህ ሲሉ የህይወት ተሞክሯቸው ያለንፍገት ለተደራሲያን እንዲደርስ ይተርካሉ። እንደማንኛው ሰው ነገን የተሻለ የማድረግ ህልም አላቸው፤ ግን ደግሞ የአካባቢያቸውን እንዲያውም በእጃቸው ላይ ያለውን ሀብትና ፀጋ ምን እንደሆነ ማየትና መለየት ተስኗቸው በከንቱ ማስነው እንደነበር በትዝታ ምልሰት እያስታወሱ የህይወት ተሞክሯቸው ያስረዳሉ።

የትውድ ቀያቸውን ጭልሻን የኋሊት እያዩ  ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ያውም በእግር ለቀው  ለመሄድ የወሰኑት ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር። የጉዟቸውን መዳረሻ ያደረጉት ደግሞ  የደቡብ  ኦሞዋን ፈርጥ ጂንካ ከተማን ነው። ግን ደርሰው ለጊዜው እንኳን የሚያርፉበት የእኔ የሚሉት ዘመድ ወዳጅ አልያም ጓደኛ አልነበራቸውም።በኪሳቸውም አይደለም የትራንስፖር ለዕለት ጉርስ የሚሆን በቂ ቤዛቢስቲን አልያዙም፤ ብቻ እግር ወደመራቸው የህይወት ዕጣ ፈንታን እንደ አመጣጡ ተቀብለው ለመቋደስ የእግር ጉዟቸውን መም አንድ ብለው ተለሙ። አቀበት ቁልቁለት የበዛበትን የ90 ኪሎ ሜትሩን ጉዞ በድፍረት ተያያዙት። በመሸባቸው ሁሉ እባካችሁ የመሸብኝ እንግዳ ነኝ፤ አሳድሩኝ እያሉ ጠየቁ። ደጋግ፣ እንግዳ አክባሪና ተቀባይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ኸረ ቤት የፈጣሪነው እደሩ  ብለው ቤት ያፈራውን አቋድሰው እየሸኟቸው ከቀናት እልህ አስጨራሽ የእግር ጉዞ በኋላ ካሰበቡት ጂንካ ከተማ ደረሱ።

ጂንካ እንደደረሱም ለከተማዋ እንግዳ፤ ለነዋሪው ባይተዋር፤ በመሆናቸው የሚይዙት የሚጨብጡት የሚያደርጉት ሁሉ ጠፍቷቸው ግራ ተጋቡ፤ የመጨረሻ ማረፊያቸው ጎዳና ሆነ። ህይወትን በጂንካ ለመግፋት የጉልበት ስራ ጀመሩ። በጉልበት ስራ የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ በመሆኑ ቤት ተከራይቶ ለመኖር አቅም ስላነሳቸው፤ ከቀን ሀሩር ከሌሊት ቁሩ እየታገሉ የጎዳና ላይ ውሎ አዳር ህይወትን አንድ ሁለት እያሉ እየተላመዱት መጡ። ቀን ቀናትን፣ ቀናት ሳምንታትን፤፤ ሳምንታት ወራትን፤ ወራት ዓመታትን እየወለዱ ጊዜው እንደዋዛ እየነጎደ፤ ያለሙት ሳይሰምር የዛሬው ቀፍጣና እና ግንባር ቀደም አርሶ አደር ቲቲዮስ የዕለት ጉርስን ለማግኘት ከህይወት ጋር እየታገሉ ድፍን ሶስት ዓመታትን በጎዳና ሻል ሲልም ከቤቶች ታዛ ስር እየተጠለሉ አሳለፉ። 

አርሶ አደር ቲቲዮስ እንዳሉት ከዕለታት አንድ ሌሊት ከእንቅልፋቸው ያነቃቸው ሀሳብ ወደ እዕምሯቸው ይመላለስ ጀመር። ሃሳቡ "ቆይ በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ነው ምዳክረው፤ እስከ መቼ ነው ዕድሜዬን በጎዳና ህይወት የማሳልፈው" የሚል ነበር። ይህን ሃሳብ ሲያወጡ ሲያወርዱ፤ ሲብሰለሰሉ ቆይተው ከአንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። "አባቴ ሰፊ የእርሻ መሬት አለው፤ ይህ መሬት ጦሙን ከሚያድር ወደ ትውልድ መንደሬ ተመልሼ ለምን አላርስም? እስካሁን ማረስ ብችል ኖሮ ለዚህ እንግልት አልዳረግም ነበር" የሚል ነበር። ከራሳቸው ጋር ብዙ ከሞገቱ በኋላ ከውሳኔያቸው ጋር  ተስማምተው ከዕለት ጉርስ ቆጥበው ያጠራቀሙትን  ጥቂት ገንዘብ ወደ ትውልድ ቀያቸው ይዘው ተመለሱ። 

ከትውልድ መንደራቸው እንደደረሱም አባታቸው የሰጧቸውን 8 ጥማድ የእርሻ ማሳ መሬት ማረስ ጀመሩ። በማሳው ላይ ምን ማልማት እንዳለባቸው ገና አልወሰኑም ነበር፤ በቂ ግንዛቤም አልነበራቸውም። በአካባቢው የተመደቡ የግብርና ባለሙያዎች በምርምር የተገኙ የተሻሻሉ የአፕል ዝሪያዎችን ቢያለሙ የአካባቢው አየር ፀባይ  ለአፕል  ልማት ተስማሚ በመሆኑ  ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ምከር ለገሷቸው።


 

ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክረ-ሀሳብ መሰረት ተዳፋት የሆነው የእርሻ ማሳቸውን ለአፕል ልማት ያዘገጃጁ ጀመር። በአካባቢው የአፕል ልማት ስለማይታወቅ አፕል ልተክል ነው ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ይስቁበቸው ጀመር። ከአፕል ይልቅ በቆሎና መሰል የጥራ ጥሬ እህሎችን ቢያለሙ ይሻላል ሲሉ ከራሳቸው ልምድ ተነስተው ምክር ለገሷቸው። በአካባቢው የማይታወቅ እንግዳ ተክል አልምተው እጠቀማለሁ ሲሉ ማሰባቸው በራሱ የዋህነት መሆኑንም እንደቀልድ አዋዝተው እንደነገሯቸው አርሶ አደር ቲቲዮስ ያስታውሳሉ።

ጥሮ ግሮ የመለወጥ ራዕይ የሰነቁት አርሶ አደር ቲቲዮስ ግን ለዚህ ምክረ-ሃሳብ ጆሮ ከመስጠት ይልቅ የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው ከአባታቸው ያገኙትን ስምንት ጥማድ ማሳ በአፕል ተክል ማልማት ጀመሩ። የተከሉት የአፕል ተክልም በጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘቱንና ፍሬ መያዝ መጀመሩን ለተመለከቱት የአካባቢው አርሶ አደሮች ግርምት ከመፈጠር አልፎ ተአምር  ሆነባቸው።

በመጀመሪያው ዓመት  88 ኩንታል የአፕል ምርት አገኙ። አንዱን ኩንታል አፕል በ3 ሺህ 500 ብር ሸጠው አይደለም ሊቆጥሩት አይተውት የማያውቁትን ከ300 ሺህ ብር በላይ አንድ ሁለት ብለው ቆጥረው ኪስ የሚሞላ ህይወት የሚቀይር ገቢ ማግኘት ቻሉ። ከአፕል ምርት ሽያጭ ባገኙት ገቢም ጎጆ ቀልሰው፤ የትዳር አጋራቸውን አግኝተው  ወልዶ ለመሳም  በቁ። "ስባክን የኖርኩት በእጄ ያለውን ፀጋ ማየት ሳላልቻልኩ ነው" ሲሉ ያለዕውቀት በከንቱ ባሳለፉት ጊዜያት ተቆጩ። "ስራ አጣሁ፤ በእጄ ገንዘብ የለም ብሎ ከማማረር የተሰጠንን ሀብትና ፀጋ በመለየትና በማልማት መለወጥ እንደምንችል ማሰብ አለብን ሲሉም ይመክራሉ አርሶ አደር ቲቲዮስ።

አሁን በፈጣሪ እርዳታ ያለኝን ዕድል ማየት በመቻሌ "ከጎዳና ህይወት ወደ ሀብት ጎዳና" ተያይዥያለሁ ይላሉ አርሶ አደር ቲቲዮስ። ጎዳናንም መርጬ ነው፤ የሀብቱንም ጎዳና መርጬ ነው፤ ለዚህ ሁሉ ግን የተሰጠንን የፀጋ መጠቀመና ራስን ለመለወጥ መጣር የስኬት ሁሉ ቁልፍ ነው ሲሉም ይመክራሉ።  ሁላችንም የራሳችን የሆነ  ፀጋ አለን፤ ዕድሎቻችን በሌሎች ሰዎች እንደተያዙ ከማሰብና ስራ ፈልጎን ቤት ድረስ አንኳክቶ እስኪ መጣ ከመጠበቅ ይልቅ በትምህርት፣በእርሻ ፣ በንግድና በመሰል መስኮች የተሰጠንን ፀጋ ተጠቅመን ሰርተን ለመለወጥ መጣር አለብን ሲለም ምክራቸውን ያክላሉ። የአርሶ አደር ቲቲዮስ ቆራጥ ውሳኔ፣ ቁርጠኝነትና  ተግባር በአካባቢው አርሶ አደሮች ተቀባይነት አግኝቶ በአፕል ልማት በስፋት በመሳተፍ እያገኙት ባለው ገቢ ኑሯቸው በእጅጉ እየተለወጠ መሆኑን ያስረዳሉም።

የደቡብ ክልላዊ የበልግ ወቅት የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ ጭልሻ ቀበሌ ''እንዳክ'' ተፋሰስ በቅርቡ ተካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ አንደኛ ሸናሌ የአርሶ አደር ቲቲዮስ መንግሥቱን የአፕል ማሳ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፤ የአርሶ አደሩ ተሞክሮ ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆን አመላክተው  አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አንደኛ  ገለጻ በአሁኑ ወቅት ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት በገጠር የሚገኘውን ሰፊና ለም መሬት ማልማት የሚችል የሰው ኃይል እንዲቀንስ አድርጓል። በገጠር ያለውን ለም መሬትና ሌሎች አማራጮችን ማየት ቢቻል በቂ ሀብት ማፍራትና መጠቀም ይቻላል ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎችን በጋ ከክረምት ማልማት የሚያስችሉ ወንዞች ቢኖሩም፤ አልምቶ ከመጠቀም አኳያ ብዙ ክፍተቶች አሉ። ለወጣቶች በተለይ ለአርሶ አደሩ ልጆች እየተፈጠረ ባለው ግንዛቤ በትምህርት የቀሰሙትን እውቀት ተጠቅመው አካባቢያቸውን እንዲያለሙ ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል። በሰብልና በፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራም ነው።

ክልሉ በፍራፍሬ ልማት ያለውን ፀጋ በአግባቡ ለመጠቀም ልዩ ፕሮጄክት ተቀርፆ በከፍተኛ ንቅናቄ ወደ ተግባር መግባቱን አቶ አንደኛ ያነሳሉ። በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት በክልሉ በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለሶስት ዓመታት የሚተገበር የ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮግራም መጀመሩን ይናገራሉ። በፕሮግራሙ አንድ አርሶ አደር በመጀመሪያው ዓመት የ30 የፍራፍሬ ተክሎች ችግኞችን በማሳው የሚያለማ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዓመት 40፣ በስሶተኛው ዓመት ደግሞ 30 በድምሩ በሶስት ተከታታይ ዓመታት የ100 የፍራፍሬ ተክሎች እንዲኖሩት እየተሰራ ነው። ፕሮግራሙን ለማሳካት ከተያዙ ስልቶች የማህበረሰቡን ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም አልምቶና ተንከባክቦ የፍራፍሬ ምርታማነት ለማሳደግ በምርምር የወጡ የተሻሻለ ዝርያዎች ማቅረብ ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮችን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳደጉ ከ67 ሚሊዮን  በላይ የፍራፍሬ ችግኞች በፕሮግራሙ  በዘንድሮው የበልግና የክረምት ወቅት ይተከላሉ። ከመካከላቸው 32 ሚሊዮን የሚጠጉት በተያዝው የበልግ ወቅት ቀሪዎቹ ደግሞ በክረምቱ ወራት እንደሚተከሉም ገልጸዋል።

የፍራፍሬ ችግኞቹ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የአፈር ለምነትን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን እና የአካባቢውን ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ የላቀ ጠቀሜታው ያላቸው መሆኑን አቶ አንደኛ ይገልጻሉ። በፕሮግራሙ ለአካባቢውን ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የፍራፍሬ ተክሎች የሚለሙ ሲሆን፤ በደጋው አፕል፣ በቆላና መስኖ-ገብ በሆኑ አካባቢዎች ሙዝና ፓፓያ፣ በወይና ደጋው አቮካዶ እንደሚለማ ገልፀዋል። በፕሮግራሙ የሚሳተፉ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከዚህም ባሻገር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከ1 ሺህ እስከ 10 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ይላሉ።

በአካባቢያችን ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በአግባቡ በማየት ዛሬ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ወደጎን በመተው ነገን በሚያልም ተስፋ ወደስራ የገቡ እጆች ከራስ ተርፈው ምርትና ትርፋማነት እያሳዩን በመሆኑ የሰጡትን የሚያበቅል ሰፊ ለም መሬትና የተትረፈረፈ የውሃ አማራጮችን ይዘን በድህነት መኖርን አብቅቶ ታሪክ መሆን አለበት። የአርሶ አደር ቲቲዮስ መንግሥቱን የህይወት ተሞክሮን ቀምረን፣ አስፍተንና ወደ ሁሉም አስርፀን  መሶባችን ሞልቶ ከምግብ ፊጆታ አልፎ ምርትን በጥራትና በብዛት ለገበያ በማቅረብ የዋጋ ንረትን በማርገብ   የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ቀን ከሌሊት ተግተን ልንሰራ ይገባል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም