የአርቲስት ሒሩት በቀለ ስርዓተ ቀብር የፊታችን ሰኞ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
የአርቲስት ሒሩት በቀለ ስርዓተ ቀብር የፊታችን ሰኞ ይፈጸማል
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2015(ኢዜአ):- የአንጋፋዋ ድምጻዊት ሂሩት በቀለ ስርዓተ ቀብር የፊታችን ሰኞ በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር እንደሚፈጸም የቀብር ስነ-ስርዓት አስፈጻሚ ኮሚቴው ገለፀ።
አንጋፋዋ ድምጻዊት ሂሩት በቀለ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ በተወለደች በ80 ዓመት ዕድሜዋ በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
የድምጻዊቷን የቀብር ስነ-ስርዓት የሚያስፈጽመው ኮሚቴ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የሂሩት በቀለ አስክሬን የፊታችን ሰኞ ሻላ መናፈሻ ጀርባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ሽኝት ከተደረገለት በኋላ ወደ ወዳጅነት አደባባይ እንደሚያመራ ገልጿል።
የኮሚቴው አባል ኮማንደር ሊቀመኳስ አየለ በወዳጅነት አደባባይ በሚኖረው መርሐ-ግብር በመሰረተ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን አማካኝነት የፀሎት ስነ-ስርዓት፣ የአበባ ማስቀመጥና የታዋቂ ሰዎች ንግግር ይደረጋል ብለዋል።
በመጨረሻም የፊታችን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጉለሌ በሚገኘው ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ስርዓተ ቀብሩ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
የኮሚቴው አባልና የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ፤ ድምጻዊት ሒሩት በቀለ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ዘመን ተሻጋሪ እና ትልቅ አሻራ ያስቀመጠች የጥበብ ሰው ናት ብሏል።
አርቲስት የህዝብ በመሆኑ፤ ድምጻዊቷ ላበረከተችው የጥበብ ስራ ተገቢውን ክብር ለመግለጽ መላው የጥበብ ቤተሰቦችና ህዝብ በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝቶ አሸኛኘት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
ሌላው የኮሚቴ አባል ፓስተር ሳሙኤል ገረመው በወዳጅነት አደባባይ በሚደረገው የቤተ ክርስቲያን የጸሎትና ዝማሬ ስነ-ስርዓት መላው የወንጌል አማኞች እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚቴው የአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ ለመርሐ ግብሩ ትብብር ያደረጉ አካላትን አመስግኗል።
ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ውስጥ ያሳለፈችው ድምጻዊት ሒሩት በቀለ በ1949 ዓ.ም ወደ ሙዚቃው ዓለም እንደገባች የሕይወት ታሪኳ ያስረዳል።
ከሀገራችን ተወዳጅና ስመጥር ድምፃውያን አንዷ የሆነችው ሂሩት በቀለ፣ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተች፣ 14 ካሴቶች ያስቀረጸች ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከ38 በላይ ሙዚቃዎች በሸክላ የታተሙ ናቸው።
ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የሙዚቃ ስራ ያቆመችው ድምጻዊት ሂሩት የሰባት ልጆች እናት፣ የአስር ልጆች አያት እና የሰባት ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።