በአገሪቱ የሕዋ ሳይንስ ግንዛቤ ለማጎልበትና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ የሕዋ ሳይንስ ግንዛቤ ለማጎልበትና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስ ግንዛቤ ለማጎልበትና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤዉን ዛሬ አካሂዷል።
በጠቅላላ ጉባኤው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ አባላቶቹ፣ የቦርዱ አባላትና የአስተዳደር አካላት ተገኝተዋል።
በጉባኤው ላይ ሳይንሳዊ ገለፃዎችና የሶሳይቲዉ የ18 አመታት ጉዞ በቦርዱ ሰብሳቢ መሰንበት ሸንቁጤ ተዳሷል።
በዚህም ሶሳይቲዉ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮችና የሰራቸውን ውጤታማ ሥራዎች ቀርበዋል።
በማብራሪያቸው ሶሳይቲው በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ትምህርትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሳይንሳዊ ልህቀትን ለማጎልበት ከህዋና ጠፈር ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በመስጠት በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ለማጎልበት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ለተማሪዎቹ የውጭ ትምህርት እድል በማመቻቸት አገሪቱ በዘርፉ ያላትን የሰው ሃይል እንዲጎለብት ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ሶሳይቲው የወደፊቷን ኢትዮጵያ በህዋ ቴክኖሎጂ እድገት የሚቀርፅ የበለፀገ የጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ሥራ አስኪያጅ ብሩክ ተረፈ በበኩላቸው የህዋ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን በአገሪቱ ለማስተዋወቅ እየተጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኅብረተሰቡን የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በተለይም የክረምት የተማሪዎች የህዋ ሥልጠና መርሃ ግብር አንዱ መሆኑን አንስተዋል።