ቀጥታ፡

በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የስኳር ምርት ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2015 (ኢዜአ) በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የስኳር ምርት ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርት ሙሉ በሙሉ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ገለጸ።  

በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የስኳር ምርትን አሁን ካለበት 3 ሚሊዮን 640 ሺህ ኩንታል ወደ 13 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።

በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ ለኢዜአ  እንደገለጹት የአገር ውስጥ የስኳር ምርትና አቅርቦት ከፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።  

ይህንንም ተከትሎ የስኳር ምርት አቅርቦትንና ፍላጎትን ለማጣጣም በማሰብ መጋቢት 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እንደገና መቋቋሙን ገልጸዋል። 

ኢንዱስትሪ ግሩፑ እንደገና ሲቋቋም የአገር ውስጥ የስኳር ምርት ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርት ማሟላት የሚያስችለውን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።  

በዚህም ለሸንኮራ አገዳ ምርት መቀነስና ለማምረቻ ወጪ መናር ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫን ተመላክቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በአዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች የመስኖ መሰረተ ልማት ለማስፋትም ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።  

በዚህም ከ2020 ዓ.ም ጀምሮ የስኳር ምርት ፍላጎትን በአገር ውስጥ በመተካት ከውጪ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት። 

ፋብሪካዎች ራሳቸው ከሚያለሙት የሸንኮራ አገዳ ምርት በተጨማሪ በአካባቢያቸው የሚገኙ አርሶ አደሮችና ማኅበራት የሚያለሙትን የሸንኮራ አገዳ በመግዛት ለግብዓትነት የመጠቀም ልምድ መኖሩንም ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም አገዳ አምራች አርሶ አደሮችና ማኅበራት ለሚያመርቱት ምርት ተመጣጣኝ ገቢ እንዲያገኙ ቀደም ሲል ከሚሸጡበት የዋጋ ተምን ከ145 እስከ 206 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማሻሻያ መደረጉንም ተናግረዋል።   

ይህም ለፋብሪካዎች በቂ ግብዓት በማቅረብ የተያዘውን የአምስት ዓመት ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። 

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች መኖራቸውን ገልጸው በእነዚህ ፋብሪካዎች በመጪው አምስት ዓመታት በዓመት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስኳር ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገሪቱ አሁን ላይ ከሰም፣ ወንጂ ሸዋ፣ አርጆ ደዴሳ፣ ኩራዝ 02፣ ኩራዝ 03፣ በለስ ቁጥር 1፣ መተሐራና ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም