ዓለም ባንክ ከ56 ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም ባንክ ከ56 ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2015 (ኢዜአ)፦ ዓለም ባንክ ከ56 ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ሀይል Xንዲያገኙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ ተገለጸ ።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በትብብር ለመስራት የጀመራቸው ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥሪ የተደረገው የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋማዊ አቅምን ለማዘመን በግዢ፣ በአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች አስተዳደር እንዲሁም በተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ የትኩረት ነጥቦች ላይ ያዘጋጀውን ስልጠና ሲከፍቱ ነው።
ባንኩ የጀመራቸውን ቁልፍ ድጋፎች አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል።
በዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ፕራክቲስ ማናጀር ኤሪክ ፈርንስትሮም በበኩላቸው ባንኩ ከ56 ሚሊዮን የሚልቁ ኢትዮጵያውያን የሀይል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ሥራዎቹን ለማቀላጠፍ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች በቅርበት በመነጋገር መፍታት ይገባል ብለዋል።
የተዘጋጀው ስልጠናም ስልታዊ ዕሳቤን ለማሳደግና በጋራ ለመስራት እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕላኒንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አንዷለም ሲዓ ተቋሙ በሦስት ዓመታት ውስጥ በኃይል ማመንጨት፣ በማስተላለፊያ መስመር እና በማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ለማከናወን የያዘውን ዕቅድ አቅርበዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሥልጠና ላይ በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።