ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ያሻል የሚል ጠንካራ አቋም አላት--ምክትል አፈ-ጉባኤ ዛህራ ሁመድ

አዲስ አበባ ግንቦት 05/2015(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ያሻል የሚል ጠንካራ አቋም እንዳላት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ገለጹ።

የአፍሪካ አገራትና የአረቡ ዓለም ምክር ቤቶች ጉባኤ(አሴካ) በኪንግደም ኦፍ ስዋቲኒ (በቀድሞ ስሟ ስዋዚላንድ) እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ የሚገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ንግግር አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ያሻል የሚል ጠንካራ አቋም በመያዝ ለእሳቤው ተግባራዊነት አበክራ እየሰራች እንደምትገኝ ምክትል አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።

በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነትም አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካ ማዕቀፍ ስር እልባት ሊያገኙ ይገባል የሚል የቆየ የኢትዮጵያ አቋም የተንጸባረቀበት ነው ብለዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ለማጽናት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ላይ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው ርብርብ ለአሴካ አባል አገራትም ሆነ ለሌሎች አገራት መልካም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2030 የዘላቂ የልማት ግቦችን፣ የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመለክት መሆኑን ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከአሴካ ጋር ያላትን አዎንታዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም