ባህሎችና ቋንቋዎችን በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራ መሆኑን ወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ባህሎችና ቋንቋዎችን በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራ መሆኑን ወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
ደሴ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ) ፡- ባህሎችና ቋንቋዎችን በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራ መሆኑን ወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
"ቋንቋና ባህል ለጋራ መግባባት" በሚል መሪ ሃሳብ 6ኛው አገር አቀፍ የቋንቋና ባህል አውደ ጥናት ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ተጀምሯል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ እንዳሉት የተለያዩ ባህልና ቋንቋዎችን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አብሮነት መጠበቅ ይገባል፡፡
"ዩኒቨርሲቲው ባህሎችና ቋንቋዎች ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነው" ብለዋል ።
በዩኒቨርሲቲው የባህል፣ ቋንቋ፣ ኪነ ጥበብና ሀገር በቀል እውቀቶች ተቋም ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
በወሎ የሚነገሩ የአማርኛ፣ አርጎብኛ፣ ኽምጢኛና ሌሎች ቋንቋዎችን በመጠብቅና በጥናት በመሰነድ ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቋንቋና ባህል ለሰላም እሴት ግንባታና ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ሚና በወጉ እንዲወጡ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትርና ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ በበኩላቸው "ውብና ቱባ ባህልና እሴቶቻችን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
"ዘላቂ ሰላም የሚፈጥሩ ሀገር በቀል እውቀቶች እየተዘነጉ በመሆናቸው ተሰንደውና ተዋውቀው የችግሮቻችን መፍቻ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል" ሲሉም አክለዋል።
''የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ ባህሎችና እሴቶች መሸርሸራቸው እየገጠሙን ላሉ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ናቸው'' ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀቶች ጥናትና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ናቸው፡፡
"ባህሎች፣ ቋንቋዎችና እሴቶች ተጠብቀውና ለትውልድ ተላልፈው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ሁላችንም የየድርሻችንን ልንሰራ ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል፡፡
የቋንቋና የባህል ሀብቶቻችን እየጠፉና እየተመናመኑ እንዲሁም በመጤ ባህሎች እየተበረዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ መጤ ባህሎችን በመከላከል የራስን ማጎለበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለሁለት ቀን በሚቆየው ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን ከአስር በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የወጣው መርሀ ግብር አመላክቷል።