ምሁራን ለአገር ዘላቂ ሰላም በእውቀትና ምርምር የታገዘ መፍትሔ በማምጣት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል- ዶክተር ፍሬው ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን ለአገር ዘላቂ ሰላም በእውቀትና ምርምር የታገዘ መፍትሔ በማምጣት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል- ዶክተር ፍሬው ተገኘ
ባህር ዳር ግንቦት 4/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው ጥረት ምሁራን በእውቀትና በምርምር የታገዘ መፍትሔ በማምጣት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ አመለከቱ።
ዩኒቨርሲቲው "የሰላም ግንባታና መልሶ ማቋቋም" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው 10ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ሳይንስ ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ እንዳሉት፤ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ከተፈጠሩም በኋላ ፈጥኖ ለማስቆምና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ምሁራን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ምሁራን የግጭት ምንጭን ለማድረቅና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያስችል የጥናትና ምርምር ስራዎች በማከናወን ሰላማዊ፣ደስተኛና የበለጸገ ሕዝብ እንዲኖር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲውም በውይይት የዳበሩ መፍትሔ ጠቋሚ የምርምር ስራዎችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አያሌው አባተ በበኩላቸው በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን የሚሰሩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ምሁራንን ጨምሮ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
መንግስት ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሰላምን ዘላቂ ለማስፈን፣የአገር ግንባታን ለማጠናከርና የሽግግር ፍትህን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"የሽግግር ፍትህ ተቋማትን ለማጠናከር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና አካታች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ምሁራን በሂደቱ በመሳተፍ የቀጣዩን ዘመን ብሩህ ማድረግ ይገባቸዋል" ብለዋል።
የጀርመን 'ፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግ' ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሱዛን ስቶልሬይተር እንዳሉት፣ኢትዮጵያ ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የራሷ ባህል፣ ወግና ታሪክ ያላት አገር ናት።
የራሷን ዘላቂ ሰላም በመገንባት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናና በዓለም አቀፍ ሰላምን በማስከበር ልምድ እንዳላትም አውስተዋል።
ፋውንዴሽኑ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን እንቅስቃሴና በምርምር የታገዘ የችግር አፈታት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ዲን ዶክተር ታዬ ደምሴ በበኩላቸው በኮንፈረንሱ ሰላም ግንባታና መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮሩ ከ12 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
"ግኝቶችን መሰረት ያደረገና ለፖሊሲ የሚሆን ግብአት ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብ ይደረጋል" ብለዋል።
እስከ ነገ በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ምሁራን፣የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።