ቀጥታ፡

የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አዲስ አበባ ግንቦት 04/2015 (ኢዜአ)፡- የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

አንዳንድ የውጭ ባለሃብቶች አገር ለቀው ሄደዋል በሚል በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ዓለም አቀፍ ክስተቶችና የውስጥ ግጭቶች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በአግባቡ ለማስተዋወቅና ባለሃብቶችን ለመሳብ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

ነገር ግን በፈተናዎች ውስጥ በተሰሩ ሥራዎችና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በዘርፉ ህጎች መሻሻላቸውና አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው እንዲሁም የመንግሥት ቁርጠኝነት ለተመዘገቡ ውጤቶች አይነተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዚህም የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የመሳተፍ ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል።

በተለይ በቅርቡ የተደረገውን የሰላም ስምምት ተከትሎ ባለው ምቹ ሁኔታ የውጭ ባለሃብቶች በአገር ውስጥ የመሰማራት ፍላጎት በአስር በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መሳብ መቻሉን ተናግረው፤ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጸጻር የአስር በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

168 ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው በግብርና፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በኢነርጂ፣ ቱሪዝምና በሌሎችም የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍስስ የቅድመ ተግበራ ሥራቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ‘’"ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023 ፎረም"’ በሚል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ዓለማቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከተለያዩ የውጭ አገራት ከመጡ ባለሃብቶች ጋር ሥምምነት መፈረሙን አብራርተዋል።

ባለሃብቶቹ ከህንድ፣ ከቻይና ከኬንያና ከሌሎችም አገራት የመጡ ሲሆን 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ሥምምነት መደረጉንም ጠቁመዋል።

መንግሥት በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።

በቅርቡ በአንዳንድ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች የውጭ ባለሃብቶች ከአገር እንዲወጡ ተደረጎል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ጠቁመዋል።

አንድም ባለሃብት ለኮሚሽኑ ያቀረበው የኢንቨስትመንት ይቋረጥልኝ ጥያቄ አለመኖሩን ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኮሚሽኑ ጋር ባደረገው የዘጠኝ ወር አፈጻጻም ግምገማ የውጭ ባለሃብቶች ከአገር ወጥተዋል ወይ በሚል ለተነሳ የግልጽነት ጥያቄ ማብራሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ነገር ግን ጥያቄውን ብቻ ነጥሎ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም