በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ80 በላይ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ፈቃድ ተሰረዘ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ80 በላይ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ፈቃድ ተሰረዘ
አዳማ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከ80 በላይ የወርቅ ማዕድን አዘዋዋሪዎችን ፈቃድ መሰረዙን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ዕምነበረድ፣ብረትና ሌሎች የማዕድናት ሀብት በስፋት እንደሚገኙ ቢሮው ይገልጻል።
የማዕድን ሀብቶቹን በአግባቡ ለመጠቀምና ከዘርፉ ኢትዮጵያን የምታገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና በዚህ ረገድም በወርቅ ማዕድን ዘርፍ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን የቢሮው ኃላፊ አቶ ካሚል አህመድ ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ 100 የሚጠጉ ልዩ አነስተኛና ሁለት ከፍተኛ ወርቅ አምራቾችና
ወርቅ ከአምራቹ ተረክበው ወደ ባንክ የሚያስገቡ ከ250 በላይ ፈቃድ ያላቸው የወርቅ አዘዋዋሪዎች በክልሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ይሁንና የወርቅ አዘዋዋሪዎች በገቡት ውል መሰረት ወርቅን ወደ ባንክ ከማስገባት ይልቅ ወደ ጥቁር ገበያ የመውሰድ ችግሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ይህንን ተከትሎ በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ያሉት አቶ ካሚል በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በገቡት ውል መሰረት ወደ ባንክ የወርቅ ማዕድንን ያላስገቡ ከ80 በላይ አዘዋዋሪዎች ፈቃድ መሰረዙን ጠቁመዋል።
ሕጋዊ ስርዓቱን በማይከተሉ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ላይ በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ነው ያሉት።
ከሕግ ማስከበሩ ጎን ለጎን ወርቅ አምራቾቹ በቀጥታ ወደ ባንክ እንዲያቀርቡ የተዘረጉ አሰራሮችን የመተግበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ሕገ-ወጥ የወርቅ ማዕድን ዝውውርን ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።