ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ በፍትህ ዘርፍ በአቅም ግንባታና ግንዛቤ መፍጠር የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር - ኢዜአ አማርኛ
ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ በፍትህ ዘርፍ በአቅም ግንባታና ግንዛቤ መፍጠር የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015(ኢዜአ):- ኔዘርላንድ በኢትዮጵያ በፍትህ ዘርፍ የምታደርገውን የአቅም ግንባታና ግንዛቤ መፍጠር ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር ገለጹ።
በኔዘርላንድስ የቀድሞው የአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች የግንኙነት ማኅበር የምስረታ ዝግጅት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ተገኝተዋል።
አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ባስተላለፉት መልዕክት የመንግሥትን አገልግሎት የተሳለጠ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኔዘርላንድስ መንግሥት በአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን 25 ዓመታትን የተሻገረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠና የፍትሕ ተቋማትን ዓላማ ማሳካት የሚችሉ ባለሙያዎችን ለማፍራትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።
የቀድሞው የአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ሊቀ-መንበር ዶክተር ኃይለስላሴ ገብረሥላሴ፤ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በማሰባሰብ በተለያዩ ሙያዊ መስኮች በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
እነዚህ ተማሪዎች በሙያዊ ዝግጅታቸው ትምህርትና ሥልጠና እንዲሰጡ በማድረግ ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር ዶክተር ሄንክ ቫን ደን ሄውቬል፤ በኢትዮጵያ ያለውን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው ለፍትህ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር በኔዘርላንድስ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎች እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በሕግ ትምህርት አይነቶችም ለበርካታ ኢትዮጵውያን የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ነው ጨምረው የተናገሩት።
አሁን ላይ ከ450 በላይ የፌደራልና የክልል የፍትሕ ተቋማት የሕግ ባለሙያዎችም የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በቀጣይም የሁለቱ አገራት የትምህርትና ሥልጠና ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ለዘመናት በቆየው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በግብርና፣ በትምህርትና ሥልጠና ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች አጋርነትን ያጠናከሩ ሀገራት ናቸው።