ቀጥታ፡

በቢሾፍቱ ከተማና ዙሪያው የተቋረጠውን የኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ለማስጀመር የጥገና ስራ እየተከናወነ ነው--የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015(ኢዜአ):-  በቢሾፍቱ ከተማና ዙሪያው የኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስተላልፍ መሰረተ ልማት ላይ "ዘራፊዎች" ባደረሱት ጉዳት የተቋረጠውን ኃይል መልሶ አገልግሎት ለማስጀመር ጥገና እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በተቋሙ የማዕከላዊ ሪጅን ሁለት የማስተላለፊያ መስመርና የፋይበር ኦፕቲክስ ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ደምሴ በ"ዘራፊዎቹ" ምክንያት ሁለት የኃይል ተሸካሚ  ምሰሶዎች ተቆርጠው መውደቃቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ለቢሾፍቱና ኢላላ ገዳ ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም በቢሾፍቱ ከተማና ዙሪያው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎት የሚሰጠው የኃይል መስመር ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡


 

በዚህም ምክንያት በቢሾፍቱ ከተማ በከፊል የመብራት አገልግሎት መቋረጡንና ስቲሊ አር ኤምና አቢሲኒያ የብረት ማቅለጫዎችን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ ግዙፍ ፋብሪካዎች በኃይል እጦት ስራ ለማቆም መገደዳቸውን ነው አቶ ጎሳዬ ያመለከቱት፡፡

እንደ አቶ ጎሳዬ ገለጻ፤ በማዕከላዊ ሪጅን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በ30 የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈጸመ ዝርፊያ 1 ሺህ 100 የሚደርሱ ብረቶች ተዘርፈዋል።

የወደቁ ምሰሶዎችን መልሶ በመጠገን አገልግሎት ለማስጀመር ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የተቋረጠውን ኃይል በአጭር ጊዜ ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም በአካባቢው በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የሚፈጸሙ ግለሰቦች  አገርንና ወገንን ከሚጎዳ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ሕብረተሰቡ በኤሌትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ እንዳይፈጸም በመከላከልና በዝርፊያ የተሰማሩ አካላትን በማጋለጥ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ጎሳዬ ጥሪ  አቅርበዋል።

 

      

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም