የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ሥርዓተ ቀብር የፊታችን እሁድ እንደሚፈፀም ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ሥርዓተ ቀብር የፊታችን እሁድ እንደሚፈፀም ተገለፀ
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ) የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ሥርዓተ ቀብር የፊታችን እሁድ እንደሚፈፀም የሥርዓተ ቀብሩ አስፈፃሚ ኮሚቴ ገለፀ ።
የቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴው በዛሬው ዕለት በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው አስከሬን ነገ ጧት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርስ ገልጿል።
የኮሚቴው አባል ተዋናይ ኪሮስ ኃይለሥላሴ እንደገለፀው የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው አስከሬን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ከጣሊያን ሮም ያለምንም ክፍያ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ተናግሯል።
አስከሬኑም ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ እናቱ ቤት ካመራ በኋላ ከአመሻሸ ጀምሮ በገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን የጸሎተ ፍትሐት መርሐ-ግብር እንደሚከናወን ገልጿል።
በማግስቱም ጧት በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በሙያ ባልደረቦቹና በአድናቂዎቹ ሽኝት ከተደረገለት በኋላ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ በ6 ሰዓት ሥርዓተ ቀብሩ ይፈፀማል ብሏል።
ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱ 'ሜጀር ክላርኔት' በማድረግ የተመረቀ ሲሆን የአልቶ ሳክስፎንና ክራር ተጨዋችም ነበር።
ከጋሽ ወዳጄነህ ፍልፍሉና ከጋሽ መርዓዊ ስጦት በኋላ በአስደናቂ ክላርኔት ጨዋታው የሚታወቀው ዳዊት ፍሬው በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው፣ የታላላቅ ኮምፖዘሮችን የክላርኔት ሥራዎች ተጫውቷል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ውስጥም በክላርኔት እና አልቶ ሳክስ ተጫዋችነት ለተወሰኑ ዓመታት በማገልገል በግሉ የመጀመሪያውን በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ አልበም፣ በፈለቀ ኃይሉ አቀናባሪነት ለማሳተም ችሏል።
ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ፣ በሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ከተቋቋመው የ"አዲስ አኩዊስቲክስ" ባንድ ጋር አልበም የማሳተም እና በበርካታ ሀገራት ኮንሰርት የማቅረብ ዕድል አግኝቶም ነበር።
በተከታታይ ሦስት የመሣሪያ ቅንብር ሥራዎችን በአልበም ያሳተመው ዳዊት ፍሬው ለሙዚቃ ሥራ በሄደበት ጣሊያን ሮም በ44 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በድንገት በሞት ተለይቷል።