በኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግናን ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግናን ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ የታሰበውን ብልጽግና ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት መገንባታቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያን የአምስት ዓመት የለውጥና የስኬት ጉዞ የሚዘክር መርሐ-ግብር ተከናውኗል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ መርሐግብሩ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር እስከ ህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የፖሊስ አባላት የሚመሰገኑበት ነው።
የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ስጋትን ቀድሞ በማምከን ከተከሰተ በኋላም ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ ህዝብ የጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን በማምጣት የታሰበውን ብልጽግና ማሳካት የሚያስችሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማት መገንባታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የፌዴራል ፖሊስ በህዝብ ዘንድ የነበረው አመኔታ ዝቅ ያለ እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ተቋማት ላይ በተሰራው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራ ፖሊሳዊ ሚናውን በአግባቡ መወጣት የሚችል ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።
በዚህም የፖሊስ ሰራዊቱ ለህዝብ ደህንነትና ሰላም መረጋገጥ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና እንዲኖረው መደረጉን ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል ምርምራ ዘርፍም በሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር የተመሰከረለት የወንጀል ምርምራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተጠርጣሪዎች ማሰቃያ የነበሩ እንደ ማዕከላዊ ያሉ የወንጀል ምርምራ ቦታዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ ከለውጡ በኋላ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ የወንጀል ምርምራ ስፍራ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በሙያዊ ብቃት ላይ የተገነባ የፖሊስ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሰራዊት የመገንባት ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፤ የፌዴራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚከፍል፣ ጀግና የፖሊስ ሰራዊት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፋት ሶስት ዓመታት የተከሰቱ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር በመላ ሀገሪቱ ተሰማርቶ ህዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በተደረገው ሪፎርም በዘመናዊ የፖሊስ አስተሳሰብ የተቃኘ አገልግሎት መስጠት መቻሉንም ነው የተናገሩት።
በቀጣይም ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ኃይሎችን ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመዋጋት የወንጀል ስጋቶችን የማምከን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።