ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀን በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ) የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀን "የአፍሪካ የተፈጥሮ እና ባህላዊ ቅርስ ከድንበሮች ባሻገር" በሚል መሪ ሀሳብ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በየዓመቱ ግንቦት 5 ቀን በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት የሚከበረው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀን በኢትዮጵያም በኮንሶ ባህላዊ መልካዓ ምድር ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

በክብረ በዓሉ ላይ የኮንሶ ዞን ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን በተመለከተ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሃይሉ፤ ኢትዮጵያ ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አስመዝግባለች።

በዚህም ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በዓለም አገራት በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ የሚገኙ  መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

ቀኑ የሚከበረው የቅርሶችን ብዝሃነት በመጠበቅ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በማለም መሆኑን ጠቁመዋል። 

''ካለፈው ትውልድ የተረከብናቸው ተፈጥሮአዊና ባህላዊ የቅርስ ሀብቶቻችንን እኛም በተራችን ጠብቀን ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለብን'' ነው ያሉት ።

የደቡብ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ የባህል ዘርፍ ሃላፊ አቶ አቡቶ አኑቶ በበኩላቸው፤ በዓሉ በኮንሶ ዞን መከበሩ ቅርሶቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልተው እንዲወጡ እና ይበልጥ እንዲታወቁ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 13  ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አስመዝግባለች።

ቅርሶችን ከመጠበቅ እና ተንከባክቦ ለቀጣይ ትውልድ ከማሻገር አንፃር ያሉ ውስንነቶችን ለማስቀረት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2015 በተካሄደው 38ኛው የዩኔስኮ ጉባኤ የአፍሪካ የዓለም ቅርሶች ቀን በየዓመቱ ግንቦት 5 እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም