በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አለባቸው - አፍሪካ ኅብረት - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አለባቸው - አፍሪካ ኅብረት
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ):- በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንዳለባቸው የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ አሳሰቡ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በአህጉሪቱ ወቅታዊ የሠላም ደኅንነት ጉዳዮች ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መስሪያ ቤት እየመከሩ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአፍሪካ አሁንም አሳሳቢ የጸጥታ ችግሮች እና ስጋቶች አሉ።
ሽብርተኝነት፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት፣ ሽምቅ ውጊያ፣ አመጽና ሌሎች የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች በዋናነት የአህጉሪቱን የጸጥታ ሁኔታ ማባባሳቸውን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ደግሞ የአህጉሪቱ የሰላም እጦት ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠራቸውን ነው ያስረዱት።
በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት ሰላምን ለማረጋገጥ ያወጧቸውን ስትራቴጂዎች በተከታታይ መገምገምና የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ከዚህም ባለፈ በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ሀገራት ከተናጠል ሥራዎች ጎን ለጎን ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ገቢራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ማድረግ የሚቻለው በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ሲቻል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የአፍሪካ ኅብረትም ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ዛሬ በተጀመረው ምክክር በጋራ የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ ኅብረቱ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አያይዘውም የአፍሪካ ኅብረት በሱዳን ያለምንም ቅደመ ሁኔታ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር በሰላም የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሮች እያካሄዱት ባለው ምክክር በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ፈንድን ለማጠናከርና የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያስችል ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ኅብረት በዛሬው ዕለት ለሶማሊያና ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሰላም ሂደት ድጋፍ የሚውል ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።