ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው-አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ

አዳማ ግንቦት 04/2015 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ ገለፁ።

3ኛው የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጉባኤ ''ጠንካራ የሴቶች አደረጃጀት ለጋራ ተጠቃሚነት'' በሚል መሪ ቃል በአዳማ አባገዳ አደራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

አቶ አብዱልሃኪም በዚሁ ወቅት ሴቶች መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

''ጠንካራ የሴቶች አደረጃጀት ለተጀመረው ስኬትና ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው'' ያሉት አስተባባሪው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ሴቶች ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት እንዲላቀቁ፣ ማህበራዊ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው ይበልጥ እንዲጎለብት ለማስቻል ፌዴሬሽኑ በሙሉ አቅሙ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በስሩ ያሉት አደረጃጀቶችን በማስተባበር እያደረገ ያለውን የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ አብዱልሃኪም ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ ሴቶች በልማትና ዕድገት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ፌዴሬሽኑ ሴቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ ቁልፍ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና የድርሻቸውን እንዲወጡ በማድረግ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የደም ልገሳ፣ የአቅም ደካማ ቤቶች ግንባታና እድሳት፣ ወላጅ አልባና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እገዛና ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱንም አብራርተዋል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የፌዴሬሽኑን የቀጣይ ሶስት ዓመታት የዋና ዋና ስራዎች ዕቅድ ላይ በጥልቀት በመምከር ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣልም ብለዋል።

የአባላቱን ቁጥር አሁን ካለበት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በዘላቂነት በሚያረጋግጡ ዋና ዋና ስራዎች ላይ በሙሉ አቅሙ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም፤ ፌዴሬሽናቸው የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያገዙ ገልጸዋል።

በጉባኤው የተለያዩ ክልሎች የሴቶች ፌዴሬሽኖች አመራሮች የአጋርነት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም