ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና በሙገር ሲሚንቶና ብሔራዊ አልኮል ትወከላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና በሙገር ሲሚንቶና ብሔራዊ አልኮል ትወከላለች
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015(ኢዜአ):- ሙገር ሲሚንቶና ብሔራዊ አልኮል በቱኒዚያ በሚካሄደው የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በመወከል ይሳተፋሉ።
ሻምፒዮናው በወንዶች ትናንት የተጀመረ ሲሆን እስከ ግንቦት 13 2015 ይቆያል።
የሴቶች ውድድር ዛሬ የሚጀመር ሲሆን እስከ ግንቦት 18 2015 ይካሄዳል።
በሻምፒዮናው ሙገር ሲሚንቶ በወንዶች፤ ብሔራዊ አልኮል በሴቶች ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በአራት ክለቦች ትወከላለች ተብሎ ቢጠበቅም በወንዶች ወላይታ ድቻና መደወላቡ ዩኒቨርስቲ በበጀት እጥረት ምክንያት በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፉ መግለጻቸውን አመልክቷል።
በወንዶች ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ሙገር ሲሚንቶ በምድብ አራት ከኮትዲቭዋሩ ኤኤስ ኢንጅስ፣ከቱኒዚያው ሞሉዲያ እና ከሩዋንዳው ሩዋንዳ ኢነርጂ ግሩፕ ክለቦች ጋር በምድብ አራት ተደልድሏል።
ሙገር ሲሚንቶ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰአት ከ30 ላይ ከሩዋንዳ ኢነርጂ ግሩፕ ጋር ያደርጋል።
በሴቶች ኢትዮጵያን የወከለው ብሔራዊ አልኮል በምድብ ሁለት ከወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ የኬንያው ኬንያ ኮሜርሻል ባንክ፣ከሴኔጋሉ ሳልቲግ እና ከካሜሮኑ ኤንኬቪ ካሜሮን ጋር ተደልድሏል።
የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰአት ከሴኔጋሉ ሳልቲግ ክለብ ጋር ያደርጋል።
ሙገር ሲሚንቶ ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና የተመለሰ ሲሆን ብሔራዊ አልኮል ኢትዮጵያን በሴቶች ለሶስተኛ ተከታታይ ዓመት በመወከል ይሳተፋል።
በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና በወንዶች 15 እንዲሁም በሴቶች 16 ክለቦች ይሳተፋሉ።
እ.አ.አ በ2022 በቱኒዚያ በተካሄደው የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና በወንዶች የግብጹ አል አሀሊ,፤ በሴቶች የኬንያ ኮሜርሻል ባንክ ክለብ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
በሻምፒዮናው በወንዶች ወላይታ ድቻና መደወላቡ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በሴቶች ብሔራዊ አልኮልና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያ ወክለው ተሳትፈዋል።