26 ኢትዮጵያውያን የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን  መዳኘት የሚያስችላቸውን  የብቃት ማረጋገጫ አገኙ

  አዲስ አበባ ግንቦት 4/2015 (ኢዜአ)፡-26 ኢትዮጵያውያን የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን  መዳኘት የሚያስችላቸውን የብቃት ማረጋገጫ ማግኘታቸውን  የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌደሬሽኑ አስታወቀ።

ወርልድ ቴኳንዶ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ የወርልድ ቴኳንዶ ዓለም አቀፍ የዳኝነት ስልጠና እና የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ወር በተሰጠው የዳኝነት ስልጠና 31 ኢትዮጵያውያንና 12 ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የመጡ ሰልጣኞች ተሳትፈዋል።

የእነዚህ ሰልጣኞች ውጤት ባለፈው ሳምንት ይፋ እንደሆነ ጠቅሰው፤ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውን ፈተናውን ማለፋቸውን ተናግረዋል።

በስልጠናው ከተካፈሉ አጠቃላይ የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቶች መካከል 30 የሚሆኑት ፈተናውን በማለፍ ዓለም አቀፍ ዳኝነት ላይ መሳተፍ የሚችሉበትን ነጥብ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

ፈተናውን ካለፉ ሰልጣኞች መካከል 26ቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም አቶ  ፍቅሩ ተናግረዋል።


 

በስልጠናው ወቅትም ኢትዮጵያውያን የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቶች አቅም እንዳላቸው ያሳዩበት እንደነበር አስታውስው፤ ያመጡት ውጤትም ለዚህ ምስክር ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት መሰል ስልጠናዎች በሌሎች ሀገራት ሲዘጋጁ ኢትዮጵያውያን የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቶች ብዙ ጊዜ በተለያዩ ችግሮች የመሳተፍ እድሉን ስለማያገኙ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ያሉ የኢትዮጵያ ዳኞች ቁጥር ውስን እንዲሆን አድርጎ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህ ምክንያት ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የዓለም አቀፍ ዳኝነት ሰርተፍኬት ያላቸው ዳኞች ሁለት ብቻ እንደበሩና አሁን ላይ ወደ 28 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በዳኝነት መሳተፍ የሚችሉበትን እድል እና ስፖርቱን በሀገሪቱ ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም