ቀጥታ፡

የመውጫ ፈተናን በላቀ ውጤት ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ

ባህር ዳር ግንቦት 3/2015 (ኢዜአ) ፦ በዩኒቨርሲቲው እየተደረገላቸው ያለውን እገዛ ተጠቅመው የሚሰጣቸውን የመውጫ ፈተና በላቀ ውጤት ለማጠናቀቅ እየተዘጋጁ መሆኑን የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ።

ከአምስት ሺህ በላይ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን እንዲወስዱ የሚያስችል ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑንም ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መንግስት እየሰራቸው ካሉ ስራዎች አንዱ ተመራቂ ተማሪዎች ምን ያህል ለሚሰማሩበት ሙያ ብቁ ናቸው የሚለውን ለመለየት የሚያስችል የመውጫ ፈተና መስጠት አንዱ ነው።

በመውጫ ፈተና ዝግጅት ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንዳሉት የመውጫ ፈተናው መሰጠት መጀመሩ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚባክን ጊዜ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተመራቂ የሆነው ተማሪ ዮሃንስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጸው የመውጫ ፈተና መሰጠቱ ተማሪዎች ጊዜያቸውንና አቅማቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እያስቻለ ነው።



ተመራቂ ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ በማጥናት በየትምህርት ዘርፋቸው እውቀትና ክህሎት በመጨበጥ በቀጣይ በስራው አለም ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲሰሩም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግሯል።

በዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር ምን ላይ በማተኮር መዘጋጀት እንዳለባቸው ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው ጠቅሶ፤ የሞዴል ፈተናም በበየነ መረብ በመውሰድ እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሷል።

ፈተናውም ያደረጉትን ዝግጅት የፈተሹበትና ክፍተቶቻቸውን ያዩበት በመሆኑ በቅርቡ በሚሰጠው የ2ኛው ዙር የሞዴል ፈተና ክፍተቶቻቸውን አርመው ጥሩ ውጤት በማምጣት ለዋናው ፈተና ተዘጋጅተው ለመቅረብ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግሯል።


 

ሌላዋ በዩኒቨርሲቲው የማርኬቲንግ ተመራቂ  ተማሪ ሰብለወርቅ ዮሃንስ በበኩሏ የመውጫ ፈተናውን በስኬት ለመወጣት ተገቢውን ዝግጅት በግልና በጋራ እያደረጉ መሆኑን ተናግራለች።

ከዚህ በፊት ተጨማሪ ትምህርት በመምህራን ከማግኘታቸው ባሻገር ሞዴል ፈተና በመውሰዳቸው በተግባርና በስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዳገዛቸው ተናግራለች።

አሁን ላይም በቤተሙከራ ለፈተና በተዘጋጁት ኮምፒውተሮች የተግባር ልምምድ እያደረጉ በመሆኑ የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና በስኬት ለማጠናቀቅ እንደሚያስችላቸው አስረድታለች።

ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቅድመ ዝግጅት ወቅት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአይሲቲ ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ማሩ ናቸው።

በፔዳና ፖሊ የሚገኙ ሰርቨሮች ተመጋግበው በየግቢው ያሉ ቤተሙከራዎች የሚገኙት ሁሉም ኮምፒውተሮች ከኢንተርኔት ጋር የማገናኘትና በፈተና ወቅት መብራት ቢቋረጥ ጀነሬተሮችን የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በቅድመ ዝግጅት ወቅትም ከ2 ሺህ 500 በላይ የመፈተኛ ኮምፒውተሮችን ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢንተርኔት ዝርጋታ፣ አቅሙን ማሳደግና የጎደላቸውን የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ኮምፒውተሮች የኢንተርኔት መሰረተ ልማት የተዘረጋላቸው ሲሆን በቀጣይ ቀሪዎቹን በማገናኘት ፈተናውን በስኬት ለማጠናቀቅ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ በበኩላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰጠው የመውጫ ፈተና ከአምስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስፈተን የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና መዘጋጀቱ የአገራችን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም የመንግስትም ሆነ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በትምህርት ስርዓቱ የተቀመጠውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ጨብጠው በመውጣት ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲውም የመውጫ ፈተናውን ለመስጠት ግብረ ሃይል አቋቁሞ የማስፈፀሚያ መመሪያውን እስከ ታች ድረስ በማስተዋወቅና የድርጊት መርሃ ግብር በመቅረጽ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ተመራቂ ተማሪዎችን ለማነቃቃት፣ የትርፍ ሰዓት ትምህርት በመስጠት፣ የሞዴል ፈተና በማዘጋጀት፣ መሰረተ ልማት በማሟላትና ክትትል በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመውጫ ፈተናው ከሃምሌ 5 እስከ12 ቀን 2015 ዓ.ም ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም