ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማስፋት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም መሆኑን አጠናክሮ ይቀጥላል  

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ  ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማስፋት ከኢትዮጵያ ባሻገር ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም መሆኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር መንገዱ የዓለም አቀፍ በረራ አገልግሎት ሽያጭ ማኔጂንግ ዳይሬክተር መስፍን ብሩ ገለጹ።

አየር መንገዱ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ወደ አትላንታ በረራ እንደሚጀምርም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእስያ አህጉር 37ተኛ መዳረሻ የሆነውን የፓኪስታን ካራቺ በረራ ከ20 ዓመታት በኋላ በይፋ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡

በፓኪስታን ካራቺ የበረራ ማስጀመሪያ መረሃ-ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላት ወደ ስፍራው አቅንተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የዓለም አቀፍ በረራ አገልግሎት ሽያጭ ማኔጂንግ ዳይሬክተር መስፍን ብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በአፍሪካ በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን የመሪነት ድርሻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመድገም እየሰራ ነው።

በዚህም አየር መንገዱ ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ፓኪስታን ካራቺ የጀመረው አዲስ በረራ አፍሪካ ከእስያ  አገራት ጋር ያላትን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡

ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንድታጠናክር እንደሚያግዛትም እንዲሁ፡፡

አየር  መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ያሉትን የአውሮፕላኖችና መዳረሻዎች ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዓለም ካሉ ምርጥ 20 አየር መንገዶች አንዱ የመሆን ግብ አስቀምጧል ነው ያሉት፡፡ ከእዚህ አኳያ አየር መንገዱ በመጪዎቹ አምስት ቀናት በአሜሪካ አትላንታ አዲስ በረራ

እንደሚያስጀምር ጠቅሰው፤ በቀጣይም ወደ ዴንማርክ ኮፐንሀገን በረራ ይጀምራል ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማስፋት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ተጨማሪ አቅም መሆኑን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡


 

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የገልፍ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የእስያ ቀጣና ዳይሬክተር ሰለሞን በቀለ በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ ፓኪስታን እና ሌሎች የእስያ አገራትን ከአፍሪካ ጋር በማገናኘት በኩል ግንባር ቀደም መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ስራ ይበልጥ እያደገ እንደሚሄድ በመግለጽ፣ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የመንገደኞችና የካርጎ ፍላጎቶችን ለማሟላት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የፓኪስታን ኤሪያ ኃላፊ አቶ ዮናስ ፈቃደ ወደ ፓኪስታን የተጀመረው አዲስ በረራ የገበያ ትስስርን በማጠናከር በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገራት የቱሪዝም ዘርፍን ከማስፋፋት አኳያም የላቀ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ ባሉት 144 አውሮፕላኖች ከ140 በላይ የጉዞ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም