በምዕራብ ወለጋ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአንድ ወር ውስጥ 2 ነጥብ 4 ሚሊዬን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአንድ ወር ውስጥ 2 ነጥብ 4 ሚሊዬን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ
ጊምቢ -ግንቦት 3/2015( ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን ለአንድ ወር በተካሄድ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ መርሃ ግብር 2 ነጥብ 4 ሚሊዬን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ የህብረተቡን ተሳትፎ ለማጠናከር የዞኑ የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮችን ጨምሮ ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በዞኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ታሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ላሊሴ ሽብሩ እንደገለጹት በዞኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል።
በዞኑ ባሉት ሁሉም ወረዳዎች ለአንድ ወር በተደረገ ንቅናቄ 2 ሚሊዬን 432 ሺህ 170 ብር ገቢ ተሰብስቧል ነው ያሉት።
ከዚህ በፊትም የዞኑ የመንግስት ሠራተኞች፣ አመራሮችና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዞኑ ሕዝብ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት የመንግስት ሰራተኛው አቶ ታሪኩ ሆርዶፋ በዛሬው እለትም ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም አስፈላጊ በሆነው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ወይዘሮ ሜቲ ታፈሰም እንዲሁ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀምረበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት ድገፍ ሲያደርጉ እንደነበረ ጠቁመዋል።
የግድቡ ግንባታ ፍጻሜ እከሚደርስ ድረስ እንደ አንድ ዜጋ የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።