የኢትዮጵያን የቡና ምርት ልማትና የገቢ መጠን የሚያሻሽል መመሪያ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የቡና ምርት ልማትና የገቢ መጠን የሚያሻሽል መመሪያ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የቡና ምርት ልማትና የገቢ መጠን የሚያሻሽል መመሪያ ተዘጋጀ።
የተዘጋጀው መመሪያ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስችልም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፤ መመሪያው በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ አካላትን የምርት አቅርቦትና ግብይት የተሻለ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች የታገዘና በቡና ልማትና ግብይት አስፈላጊ የሚባሉ የአሠራር ስልቶችን ያካተተ በመሆኑ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የተዘጋጀው መመሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ከቡና ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
በቡና ልማት ለሚሰማሩ አካላት ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋትና የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚጠቅም መመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቡና ልማት የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን ማጠናከርና እሴት የተጨመረበትን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዘርፉን ልማትና ግብይት በዘመናዊ አሠራር ለማምራት፣ የባለድርሻ አካላትን ትብብር ለማሳደግና የአረንጓዴ ልማትን ለመደገፍ ያግዛል ብለዋል።
ከዚህ በፊት መመሪያው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሦስተኛ ጊዜ የታተመ ሲሆን፤ በዛሬው እለት በአማርኛ ቋንቋ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በቀጣይም በአገር ውስጥ ባሉ ቡና አብቃይ አካባቢዎች በብዛት በሚነገሩ ቋንቋዎች መመሪያው እንደሚዘጋጅ ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
በዓለም ላይ አሁን ካሉት 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቡና አምራች ገበሬዎች መካከል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቡና ምርት በውጭ ምንዛሬ ግኝትም የላቀ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል።