የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እና ኦቪድ ግሩፕ ጋር በመተባበር "አዲስ አበባን በአዲስ የዲፕሎማሲ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ምሁራን፣ የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።
ከመድረኩ ታዳሚዎች መካከል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ፤ የከተሞችን ሁለንተናዊ እድገት ለዲፕሎማሲ ማዕከልነት መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት በ2063 አጀንዳው ከተሞችንና የሕዝብ መኖሪያ አካባቢዎች ዘመናዊ መሰረተ-ልማት እንዲላበሱ በማድረግ የባህልና የኢኮኖሚ መናኸሪያ እንዲሆኑ ግብ ማስቀመጡንም አብራርተዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ሕብረትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ ሁለንተናዊ ልማትና እድገቷ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር የሕንፃ ግንባታና የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት መምህሩ ዶክተር ዘገየ ቸርነት፤ ከዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከላት መካከል አንዷ የሆነችውን አዲስ አበባ ደረጃዋን በሚመጥን መልኩ እየዘመነች መቀጠል አለባት ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ ዝቅተኛ የከተማ ምጣኔ ያላት መሆኗን ጠቅሰው፤ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ማዘመንና ማስፋት ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ እየጨመረ የመጣውን ጫና ከግምት በማስገባት የሕዝብ ቁጥርን ታሳቢ ያደረገ አማራጭ የከተማ ግንባታ ማስፋት ላይ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
እያደገ የመጣውን የከተሜነት የስበት ማዕከል ታሳቢ ያደረገ የመዲናነት የልማት ሥራ በስፋት ማከናወን ይጠይቃል ብለዋል።
የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረጉ ጥረቶች የመገናኛ ብዙሃን አበርክቶ ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነቸው አዲስ አበባ የታላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም፤ በመዲናዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተሰርተው ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች ለገጽታ ግንባታና አማራጭ የቱሪዝም መስህብነት የላቀ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች መዳረሻቸውን ወደ ክልል ከተሞች እንዲያሰፉ ለማድረግ ልማቱን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፤ በአዲስ አበባ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በክልል ከተሞችም ማስፋት ይጠበቅብናል ብለዋል።
አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ፤ የአዲስ አበባን ጽዳት፣ ውበትና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሌት ተቀን እየሰሩ ያሉ ዜጎችና የመንግሥት አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትዓለም መለሰ፤ የመዲናዋን ነዋሪዎች ሕይወት ለማሻሻልና ገጽታዋን ለመቀየር ባለፉት ሦሰት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን አብራርተዋል።
በቀጣይም የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በማጽናት ሁሉንም ማዕከል ያደረጉ የልማት ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማን የዲፕሎማሲ፣ የመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሽፋንና በለውጥ ሥራ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሃሳብና አስተያየቶች ቀርበዋል።