ለኩላሊት ሕመምተኞች የሕክምና ተቋም ግንባታ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ለኩላሊት ሕመምተኞች የሕክምና ተቋም ግንባታ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ ለኩላሊት ሕመምተኞች የሕክምና ተቋም ግንባታ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ጥሪ አቀረበ።
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኩላሊት ሕሙማን ቁጥር በርካቶችን ለችግር ከመዳረጉ ባለፈ አቅምን ያላገናዘበው የሕክምና ወጪ የብዙዎችን ቤት እያንኳኳ ይገኛል።
የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለኩላሊት ሕመምተኞች የሕክምና ተቋም ግንባታ ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
መንግሥት ለኩላሊት ሕመምተኞች የሕክምና ተቋም ለመገንባት 1 ሺህ 410 ካሬ ሜትር መሬት ከስድስት ወር በፊት በነፃ ቢሰጥም እስካሁን ግንባታውን ማስጀመር አልተቻለም ብለዋል።
ድርጅቱ ግንባታውን ለማስጀመር ለበርካታ ተቋማት ጥሪ ቢያቀርብም ምላሽ የሰጡት ጥቂት ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ቢገነባ የኩላሊት ሕመምተኞችን የሕክምና ወጪ ከመቀነስ ባለፈ የንቅለ-ተከላ አገልግሎት በመስጠት እንደ አገር የገቢ ማስገኛ መሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የኩላሊት ሕመምተኞችን የዲያሊሲስ ወጪ ሙሉ በሙሉ መሸፈን የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከማዕከሉ በሚገኘው ገቢ አነስተኛ የግል ክሊኒኮችን በመደገፍ የኩላሊት ሕክምና አገልግሎቱን ማሳደግ ስለሚቻል ግንባታው እውን እንዲሆን ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በውጭ ሀገር ንቅለ-ተከላ ለሚያደርጉ ታማሚዎች፣ ኩላሊት ለጋሽና፣ አስታማሚዎች ነፃ የበረራ አገልግሎት ዕድል በመስጠቱ አመስግነዋል፡፡
ዕድሉ በወር ለ12 ታማሚ፣ ኩላሊት ለጋሽና፣ አስታማሚ ነፃ የበረራ አገልግሎት እንደሚሰጥ በመጠቆም፤ የዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑት የገቢ አቅማቸው አነስተኛ የሆነና የህመማቸው ደረጃ ከፍ ያለው ተለይተው እንደሆነም ተናግረዋል።
ማዕከሉን ለመገንባት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ሥራ አስኪያጁ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡