ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሰራቸው የማነቃቂያ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው--የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሰራቸው የማነቃቂያ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው--የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሰራቸው የማነቃቂያ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከግል ዘርፉና ከኢንዱስትሪው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር የተደረገው ንቅናቄ አበረታች መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባካሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ በጀመረው ልክ አዋጆችን እና ፖሊሲዎችን በማጠናቀቅ የተሻለ ስራ ለመስራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ አኳያ ኢንቨስትመንት ስቦ ወደ ተግባር ከገቡ በኋላ ውጤታቸውን መለካት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪው የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድምር ውጤት እንደመሆኑ የማህበረሰብ አቀፍ ልማት በማሳተፍ ማስተሳሰር እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡትⵆ
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንደሚገባ፣ ለዚህ ደግሞ የብድር አገልግሎት ከሚመለከተው አካል ጋር በመቀናጀት መፍታት ይገባል ብለዋልⵆ
አባላቱ አክለውም በአምራች ኢንዱስትሪዎች እየገጠመ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ከውጭም ከውስጥም ካሉ አካላት ጋር ትስስሮችን በማጠናከር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋልⵆ
የሀገር ውስጥ ባለኃብት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በምርምር እና በጥናት መደገፍ እንደሚያስፈልግ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እንደየዘርፋቸው ለማቀራረብ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ ብዙ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ማብራራታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታየውን እጥረት ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
ሚኒስትሩ አክለውም ኢንዱስትሪዎች ወደ ተግባር የገቡ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ስላለባቸው በቀጣይ ወደ ተግባር እንዲገቡ የማድረግ ተግባር ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋልⵆ