ቀጥታ፡

ከወራት በፊት አጋጥሞ የነበረው የደም እጥረት መሻሻል ቢያሳይም የቋሚ ደም ለጋሾች ቁጥር አሁንም አነስተኛ ነው - የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ከወራት በፊት አጋጥሞ የነበረው የደም እጥረት መሻሻል ቢያሳይም የቋሚ ደም ለጋሾች ቁጥር አሁንም አነስተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

የደም ባንኩ ባለፈው አመት 337 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ ቢችልም በተያዘው በጀት አመት ዘጠኝ ወራት የሰበሰበው 250 ሺህ ዩኒት ደም ብቻ መሆኑ ታውቋል።


 

የአፈፃፀሙ አሃዝ ያመላከተውም የዘንድሮው ዓመት የደም ለጋሾች ቁጥር መቀነሱን ነው።

በመሆኑም በደም እጥረት ሳቢያ የሚያጋጥመውን የዜጎች ህልፈተ ህይወት ለመቀነስ ደም ለጋሾች የተለመደ በጎነታቸውን እንዲያሳዩ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።

የአገልግሎቱ  ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጤናየ ደምሴ፤ የተለያዩ የአለም አገራት ተሞክሮ የሚያሳየው የደም ልገሳ ልምድ ከፍተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከወራት በፊት አጋጥሞ የነበረው የደም እጥረት መሻሻል ቢያሳይም የቋሚ ደም ለጋሾች ቁጥር አሁንም አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በደም እጥረት ሳቢያ በየጊዜው ለህልፈት የሚዳረጉ ዜጎች ወገኖች በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው ደም በመለገስ ህይወት እንዲያድኑ  ዜጎች በየሶሰት ወሩ ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በወሊድ ወቅት ከሚሞቱ እናቶች መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት በደም እጥረት ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

በተመሳሳይ የኦ ኒጌቲቭ ደም እጥረት ሁልጊዜም ያለ መሆኑን ገልጸው በአገራችን የኦ ኒጌቲቭ ደም ያላቸው ዜጎች ቁጥር 3 ፐርሰንት ብቻ በመሆኑ ችግሩን ሰፊ ማድረጉ ተገልጿል።

ከ2 ሺህ 700 በላይ የኦ ኒጌቲቭ ደም ያላቸውን ዜጎች አባል በማድረግ እጥረቱን ለመቀነስ የሚያስችል ጥረት መጀመሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም