ኢዝላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዝላማባድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመረቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015 (ኢዜአ) ፦በፓኪስታን ኢዝላማባድ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመርቆ መከፈቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኤምባሲው በይፋ መመረቅ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ግንኙነት አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑም ተገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የትብብር መስኮች ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ የመጡት ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን አዳዲስ የግንኙነት ምዕራፎችን እየከፈቱ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ካራቺ የጀመረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በኢዝላማባድ ከአንድ አመት በፊት የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋ ተመርቋል።
ኤምባሲውን መርቀው የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን ናቸው።
በኢዝላማድ ተቀማጭ የሆኑ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት የምረቃት ስነ-ስርዓት መካሄዱም ተጠቅሷል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የኤምባሲው በይፋ መመረቅ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
ሀገራቱ ከሁለትዮሽ ባሻገር በጋራ የሚሰሩባቸው በርካታ አለምአቀፍ የጋራ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸው፤ የኤምባሲው መከፈት ግንኙነቱን ለማስፋት እና ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል።
የተጀመሩ የንግድ ፣ የኢንቨስትመንት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች እንዲጠናከሩ ኤምባሲው እንደሚሰራ ጠቁመው ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጎልበት የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂና ራቢኒ ካሃን በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ተመሳሳይ የልማት እና ኢኮኖሚ ፈተና ያለባቸው ሀገሮች መሆናቸውን በመጠቆም ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ የኢትዮጵያ የኤምባሲ በኢዝላማባድ መኖር ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
ኤምባሲው ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በይፋ ለምረቃ እንዲበቃ የፓኪስታን መንግስት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ናቸው።
ኤምባሲው ለዘላቂ የሁለቱ ሃገራት ጥቅም መሰረት መሆኑንም አምባሳደር ጀማል አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1950ዎቹ ነበር።