የማዕድን ሃብት ልማት ረቂቅ አዋጅ የሀገርና ህዝብን ዘላቂ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መታየት አለበት-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ሃብት ልማት ረቂቅ አዋጅ የሀገርና ህዝብን ዘላቂ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መታየት አለበት-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ ግንቦት 03/2015(ኢዜአ)፡- አዲስ የተሻሻለው የማዕድን ሃብት ልማት ረቂቅ አዋጅ የአገርና ህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት በሚያስጠብቅ መልኩ መታየት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባው የማዕድን ልማት ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አዋጆች ላይ ተወያይቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የማዕድን ሃብት ልማት ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነትና ይዘትን በሚመለከት ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል።
መንግስት በሀገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ውስጥ የማዕድን ዘርፉን ከብዝሃ ምጣኔ ሃብት ግንባታ ዘርፎች አንዱ በማድረግና ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕድን ሀብት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በማሰብ በስራ ላይ የሚገኙ የማዕድን ዘርፍ ህጎች በጥናት ላይ የተመሰረተ ማሻሻያ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
በመሆኑም አሁን በስራ ላይ ያለው የማዕድን ስራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2002 የነበሩበትን ክፍተቶች በመሙላት እንዲሁም አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መሻሻሉን አብራርተዋል።
በቀረበው የማዕድን ሃብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት አዋጁ በኢትዮጵያ ያሉ የማዕድን ሃብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያግዝ አንስተዋል።
አባላቱ አክለውም የኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴም የማዕድን ሃብትን ከማልማት፣ ከፈቃድ አሰጣጥ፣ ከቁጥጥር፣ ከግብይት ዘላቂ ተጠቃሚነት አንጻር የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በዝርዝር እና በትኩረት ማየት እንዳለበት ተናግረዋል።
የማዕድን ሃብት አላቂ ወይም የማይተካ ከመሆኑ አንጻር አዋጁ የሀገርና ህዝብን ዘላቂ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲዘጋጅም አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ በአባላቱ የተነሱ ሃሳቦችን ጨምሮ ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር እንዲያይ ለኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው የፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ባቀረቡት ማብራሪያ አዋጁ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ አሰራር ዘዴን ተግባራዊ በማድረግ በግዥ ስርዓቱ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዱ ተጨማሪ ድንጋጌዎችን ያካተተ እንዲሆን ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ ከፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ጋር ተያይዞ ከግዥና ንብረት አወጋገድ ጋር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት ተጠያቂነት በሚያሰፍን መልኩ እንዲዘጋጅ በትኩረት መታየት አለበት ብለዋል።
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተነሱ ሃሳቦችን ጨምሮ በዝርዝር እንዲያየው ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ምክር ቤቱ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።