የኢትዮጵያና ፓኪስታንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ፓኪስታንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ፓኪስታንን የሁለትዮሽ ግንኙነት በላቀ መልኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ፓኪስታኗ ካራቺ ከተማ ከቀናት በፊት ዳግም በረራ መጀመሩ ይታወቃል።
የአየር መንገዱ ዳግም በረራ መጀመር ለሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ትብብርና በተለይም የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር የላቀ ፋይዳ አለው ተብሏል።
የአየር መንገዱ ወደ ካራቺ የመጀመሪያ በረራውን ሲያደርግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የቢዝነስ ልዑክ ወደ ሥፍራው አቅንቷል።
የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በካራቺ የተካሄደ ሲሆን በአገራቱ መካከል የትብብር ግንኙነቱን ለማጠናከር ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የኢትዮጵያና ፓኪስታን ሁለንተናዊ ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ በረራ መጀመሩ በሁለቱ አገሮች ዘንድ በተለይም የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሩን በማሳለጥ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያቸውን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ፓኪስታን የምትልካቸውን የተለያዩ ምርቶች የማሳደግ ፍላጎት አላት ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ፤ ፓኪስታንም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያላት አቅም ለኢትዮጵያ ጥሩ ዕድል ይኖረዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የወጪ ንግድን መጨመርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ የፓኪስታን ባለሃብቶች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ብለዋል።
በሁሉም መስኩ የኢትዮጵያና ፓኪስታንን የሁለትዮሽ ግንኙነት በላቀ መልኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለፓኪስታን ባለሃብቶች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፓኪስታን ንግድ ልማት ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዙቤር ሞቲዋላ፤ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ አቋም አላት ብለዋል።
ኢትዮጵያም ተመሳሳይ አቋም ይዛ እየሰራች በመሆኑ የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በፓኪስታን ካራቺ በተካሄደው የቢዝነስ ፎረም በሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያጠናክር ስምምነት ተፈርሟል።