ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የእንስሳትና የዓሳ ሃብት ልማትን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

 አዲስ አበባ  ግንቦት 3/2015 (ኢዜአ):  በኢትዮጵያ የእንስሳትና የዓሳ ኃብት ልማትን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ። 

"የሌማት ትሩፋትን በመተግበር የሥነ-ምግብ  ዋስትናን እናረጋግጣለን'' በሚል መሪ ሀሳብ የግብርና ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።  

 

በውይይቱም በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብሮች የተያዙ ግቦች፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጹሑፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።         

 

ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ. ም. በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገው የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገባው ምርት በአገር ውስጥ መተካትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ግቦችን ይዟል።    

 

አሁን ላይ ያለውን ዓመታዊ የወተት ምርት ከ6 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር የላምና ግመል ወተት ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊየን ሊትር ከፍ ማድረግ፣ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዓመታዊ የእንቁላል ምርትን ወደ 9 ነጥብ 2 ቢሊየን ማድረስ ከተያዙ ውጥኖች መካከል ይገኝበታል።      

 

በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ የዶሮ ሥጋ ምርት መጠን 90 ሺህ ቶን የደረሰ ሲሆን፤ ምርቱን ወደ 240 ሺህ ቶን ማሳደግ ሌላው የመርሃ-ግብሩ ዓላማ መሆኑም ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።  

 

ከማር ምርት ጋር በተያያዘም ዓመታዊ ምርት መጠኑ 147 ሺህ የደረሰ ሲሆን፤ የምርት መጠኑን ወደ 296 ሺህ ቶን ማድረስ፤ 78 ሺህ ቶን የዓሣ ምርትን ደግሞ ወደ 215 ሺህ ቶን ማሳደግ በሌማት ትሩፋት ከተያዙ ግቦች ውስጥ ይገኝበታል።   

 

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሕዝብ  ተወካዮች  ምክር  ቤት አፈ-ጉባዔ  ታገሰ ጫፎ፤ ኢትዮጵያ  በእንስሳትና የዓሳ ኃብት የታደለች አገር ብትሆንም ከዘርፉ ብዙም ተጠቃሚ አይደለችም ብለዋል። 

 

በመሆኑም የእንስሳትና የዓሳ ኃብት ልማትን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል። 

 

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ በኢትዮጵያ ሀገረ-ሰብ ላሞች፣ ዶሮዎችና ከፍተኛ መጠን  ያለው የንብ መንጋ ቢኖርም በቂ ወተት፣  እንቁላል፣ ማርና ዓሳ እየተገኘ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።


 

 

የገበያ መር ዘመናዊ እርባታ አለመከተል፣ ቴክኖሎጂን በበቂ መጠን አለመጠቀም እንዲሁም መኖና ሌሎች የአቅርቦት ችግር ዘላቂ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።   

 

በዘርፉ  ምርታማነትን ለማሳደግ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ተግባራዊ ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።     

 

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ከተጀመረ በኋላ በዘጠኝ ወራት ከ34 ሚሊየን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶች በዶሮ እርባታ ለተደራጁ ወጣቶች መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የንብ ቀፎዎች ለአርቢዎች መሰራጨቱንም ገልጸዋል።  

 

የወተት ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያም  1 ነጥብ 2 ሚሊየን ጊደሮችና ላሞች በተሻሻለ ዝርያዎች የማዳቀል ተግባራት መከናወኑንም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።  

 

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቲ በበኩላቸው፤ አንድ ሀገረ-ሰብ ላም በአማካይ በቀን 1 ነጥብ 5 ሊትር ትታለባለች።

 

ይህም ዝርያ ማሻሻያ ከተደረገባት ላም በ13 ሊትር ያንሳል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ ጠንካራ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።

 

በተለይም በዘርፉ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

 

የዓለም አቀፉ እንስሳት ምርምር ተቋም ተወካይ ናሙኮሎ ኮቪክ እንደተናገሩት፤  ከእንስሳት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ዝርያ ከማሻሻል ባለፈ የእንስሳት ጤና መጠበቅ ላይ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም