በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ እቅድና የአረንጓዴ አካባቢ ልማት ግብን ለማሳካት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ እቅድና የአረንጓዴ አካባቢ ልማት ግብን ለማሳካት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ የታቀደውን ንጹህ እና የአረንጓዴ አካባቢ ልማት ግብ ለማሳካት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር እስከ 2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ እንደሚያደርስና በዓመት ከ865 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል የተባለ ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት የአየር ንብረት ተለዋዋጭ መሆንና አድማሱን እያሰፋ የሰው ልጆችን እየፈተነ ነው።
በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ድርቅ የስርጭት አድማሱን እያሰፋ ስርዓተ ምህዳሩን እያዛባና ብዙ ፈተናዎችን እያስተናገድን እንገናኛለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ውይይቶች ላይ የጎላ ተሳትፎ በማድረግ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ገቢራዊ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ፖሊሲና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን ጠቅሰዋል።
የውሀና ፍሳሽ አገልግሎት፣ የሀይል ልማት፣ እንዲሁም የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች በስፋት የሚሰራባቸው ተግባራት መሆናቸውን ገልጸው፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለዓለም በተምሳሌትነት የሚወሰድ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ልማት ስትራቴጂም ጅምሮችን በማጠናከር እስከ 30 ዓመት ንጹህ እና በአረንጓዴ ልማት የተሸፈነ ስነ ምህዳር ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
በመሆኑም ስትራቴጂው ግቡን እንዲመታ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የውሀና ፍሳሽ አገልግሎት፣ የታዳሽ ኃይል ልማት እንዲሁም የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራዎች መልካም ጅምሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ልማት ስትራቴጂ ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንዲሁም ኢትዮጵያ ተግባራዊ ካደረገቻቸው የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲና የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የካርበን ልቀት ልማት ስትራቴጂን በማጠናከር እስከ 30 ዓመት ንጹህና በአረንጓዴ ልማት የተሸፈነ ስነ- ምህዳር ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ ግቡን እንዲመታ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆችን አኗኗር የሚያዛባ ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የዓለምን የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዳይበልጥ ስምምነት ላይ ደርሰው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ከመተግበር ባለፈ ለቀጣይ 30 ዓመታት የምትመራበት የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ እውን አድርጋለች ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ስትራቴጂ ገቢራዊ ሲሆን የግብርና ልማትን በማፋጠን እስከ 2050 ድረስ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት ሊባክን የሚችል 20 ሚሊየን ቶን ምርት ማዳን ይቻላል ተብሏል፡፡