ቀጥታ፡

የሀላላ ኬላ የቱሪዝም መስህብ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ መልማትና መለወጥ እንደምትችል ሁነኛ ማሳያ ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ የሀላላ ኬላ የቱሪዝም መስህብ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ መልማትና መለወጥ እንደምትችል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።


የጋራ ምክር ቤት አባላቱ የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነውንና በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻን ጎብኝተዋል።


የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በአርባ ምንጭ ከተማ የምክክር መድረክ ማካሄድ የጀመሩ ሲሆን በተጓዳኝም የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።


በዚህም መሰረት በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ ጎብኝተዋል።


የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ ከጉባዔው በተጓዳኝ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታችን የልማቱ አጋዥ ሆኖ ለመሥራት ጥሩ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

 



ከዚህም ባለፈ የምክር ቤቱ አባላት በሁሉም መስክ ተቀራርበው እንዲሰሩና የበለጠ እንዲተዋወቁ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።


የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነውን የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻ መጎብኘታችን አብሮነታችንን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ተናግረዋል።


ከሀላላ ኬላ የቱሪዝም መስህብ ጉብኝታችን የተረዳነውም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ መልማትና መለወጥ እንደምትችል ያየንበት ነው ብለዋል።


የሀላላ ኬላ ፕሮጀክት የአካባቢውን የቱሪስት ፍሰት በመጨምር የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና በሌሎች አካባቢዎችም ያሉ እምቅ ፀጋዎችን ወደ ጥቅም ለመለወጥ ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።


የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአገው ሸንጎ ሊቀ-መንበር አላምረው ይርዳው፤ ሀላላ ኬላ አስደናቂ መልክዓ-ምድር ላይ የተገነባ ዘላቂ የኢትዮጵያ ኃብት መሆኑን ጠቅሰዋል።


ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት የላቀ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው በመጥቀስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢኒሼቲቩን ወስደው በመሥራታቸው አድንቀዋል። 


የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ፈይሰል አብዱልአዚዝ፤ ሪዞርቱ በቀጣይ ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ለመሥራት በማሳያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።


የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ አመራር መሀመድ የኑስ፤ ሀላላ ሪዞርት ውሃን፣ እጽዋትንና ሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶችን የያዘ አስደናቂ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ መሆኑን ገልጸዋል።


የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር አመራር አብዱራህማን መሀዲ፤ የሀላላ ኬላ ፕሮጀክት ከቱሪዝም መስህብነቱ ባለፈ የተፈጥሮ ውበትን ያጎላና ኃብትን መጠበቅ ያስቻለ ድንቅ ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን ታፈሰ፤ የሀላላ ኬላ (የንጉስ ሀላላ ካብ) ለቱሪዝም ልማት እሴት ተጨምሮበት ለመስህብነት መዋሉ ለደቡብ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት እምርታ የሚያመጣ እንደሆነ አንስተዋል።


 


በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ በበኩላቸው፤ የሀላላ ኬላ የልማት ፕሮጀክት ኢትዮጵያ መልማት የሚችል ሰፊ አቅም ያላት መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።


በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዘጋጅነት የተደረገው የሀላላ ኬላ ጉብኝትም ፖለቲከኞች በልማትና ሌሎችም መስኮች ተቀራርበው እንዲሰሩ የሚያደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም