ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ።

በስትራቴጂው ይፋ ማድረጊያ መርሀ-ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ሚኒስትሮች እና የልማት አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር እስከ 2050 ድረስ የሚተገበር ስትራቴጂ መሆኑም ተነግሯል።

ስትራቴጂው እ.ኤ.አ 2015 ከጸደቀው የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጋር የተጣጣመ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ያዘጋጀው ይህ የልማት ስትራቴጂ በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ታላሚ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

ስትራቴጂው ከፓሪሱ ስምምነት በተጨማሪ ከሀገሪቱ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድና ሌሎች የረጅም ጊዜ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ ነውም ተብሏል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ እንዳሉት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆችን አኗኗር የሚያዛባ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ነው።

በዚህም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የዓለምን የሙቀት መጠን ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዳይበልጥ ስምምነት ላይ ደርሰው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረጓን ገልጸዋል።

ከ200 በላይ የአየር ንብረት ለውጥ ማገገሚያ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ልማት ስትራቴጂ በተሟላ መልኩ ገቢራዊ ሲሆን እስከ 2050 የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርት ዕድገት አሁን ካለው አንፃር 66 በመቶ ያሳድጋል ተብሏል።

በስትራቴጂው ትግበራ የማይበገር የግብርና ልማትን በማፋጠን እስከ 2050 ድረስ 20 ሚሊዮን ቶን ምርት ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በመታደግ ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተይዟል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም