በታንዛንያ አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጋር ውይይት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በታንዛንያ አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ ግንቦት 2 /2015 (ኢዜአ)፦ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት(IOM) የታንዛንያ ተጠሪ ዋና ዳይሬክተር ማውሪዚዮ ቡሳቲ ጋር በሀገሪቱ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን ዜጎች ወደ አገር ቤት ለመመለስ ቀደም ብሎ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
የዓለም አቀፉን የፍልሰተኞች ድርጅት ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ የገለፁት አምባሳደር ሽብሩ ዜጎች በእስር ቤት ቆያታቸው ሰብአዊ መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በእስር ላይ ረዥም ጊዜ የቆዩና ለታማሚዎች ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት አምባሳደሩ አሳስበዋል።
በታንዛንያ የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት(IOM) ዋና ዳይሬክተር ማውሪዚዮ ቡሳቲ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የብዙ ሀገር ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ታንዛኒያ ገብተው በሀገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው በተለያዩ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከኤምባሲው ጋር በቅንጅት በመስራት እና በመለየት አቅም በፈቀደ መጠን ቅድሚያ ተሰጥቶአቸው እንዲመለሱ የተቻላቸውን ያህል ጥረት እንዳደርጉ ገልጸዋል።
አምባሳደር ሽብሩ ማሞ እና ዋና ዳይሬክተሩ ወደ አገር ቤት ለመመለስ የጉዞ ሰነዳቸው በኤምባሲው እየተዘጋጀላቸው ካሉ ቁጥራቸው 60 ያህል ከሚሆኑ ዜጎች ጋር ውይይት አድርገዋል።