የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሱዳን ግጭት ተፈናቅለው ለመጡ ዜጎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሱዳን ግጭት ተፈናቅለው ለመጡ ዜጎች ድጋፍ አደረገ
መተማ ግንቦት 2/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሱዳን በተቀሰቀሰ ግጭት ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ለተጠለሉ የተለያዩ ዜጎች 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተባባሪ አቶ ግዛቸው በለጠ እንዳሉት፣ ድጋፉ የተደረገው ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር ነው።
ለተፈናቃይ ወገኖች በተደረገው ድጋፍ ውስጥ መድሃኒት፣ የህፃናት አልሚ ምግቦችን እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች መካተታቸውን ተናግረዋል።
ድጋፉ የተሰጠው በከተማዋ ለተጠለሉ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሱዳን ዜጎች መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የቀይ መስቀል ማህበር ከሌሎች ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር ቀደም ሲል 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ከተደረጉ የቁሳቁስ ድጋፎች በተለይ የመድሃኒት ድጋፉ የተፈናቃይ ዜጎችን ጤና ለመከታተል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
አስተባባሪው እንዳሉት እስካሁን ከተደረገ የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር ከ1 ሺህ በላይ ለሆኑ ተፈናቃይ ዜጎች ነፃ የስልክ አገልግሎት በመስጠት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራ ተሰርቷል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሃሊማ ሙሳ እንዳሉት፣ ከሱዳን ካርቱም ተነስተው ወደ መተማ ዮሐንስ ከመጡ ሦስት ቀን ሆኗቸዋል።
ህጻን ልጃቸው ትላንት የሰውነት ሙቀቱ ጨምሮ ተቸግረው እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ በተደረገላቸው የመድሃኒት ድጋፍ ከሕመሙ ማገገሙን ገልፀዋል።
ሌላኛው ድጋፍ የተደረገላቸው አቶ ሙሃመድ ሀሰን በበኩላቸው ከስምንት ቀን በፊት ከሱዳን ካርቱም ተነስተው መተማ ዮሐንስ ከተማ መግባታቸው ተናግረዋል።
ከሦስት ህፃን ልጆቻቸው ጋር መፈናቀላቸውን ገልጸው "ዛሬ ለልጆቼ ያገኘሁት የአልሚ ምግብ ድጋፍ እፎይታ ሰጥቶኛል" ብለዋል።
ወደ ከተማው ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያውያን እና በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እየተደረገላቸው ላለው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ የተለያየ ሃገር ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።